የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6ወር አፈጻጸሙን አጠቀላይ ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ ጥር 15/2012 ዓ.ም ገመገመ፡፡ የቀጣይ 6ወር የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም መክሯል፡፡
የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን ተቀዳሚ ተወካይ ወንድወሰን ግዛቸው የተከናወኑ ዋናዋና ተግባራትን በሪፖርት ሲያብራሩ በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃና ልማት ሥራዎች የኦቶሜሽን ትግበራን በማጠናከር የምዝገባ አገልግሎቶችን ማዘመንና የኦንላይን ምዝገባ ቅበላን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ከ WIPO፣ EPO፣ CNIPA፣ ARIPO ፣EUIPO እና ሌሎችም አቻ ተቋማት ጋር የተጀመሩ ግንኙነቶች ማጠናከር በመቻሉ በቴክኒክና ሰው ሃይል ስልጠና ድጋፎች እንደተገኙ አቶ ወንድወሰን በሪፖርቱ ተናግረዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ አእምሯዊ ንብረት ትመና እና ኮሜርሻላይዜሽን ዙሪያ በ WIPO የታተሙ የህትመት ውጤቶችን ወደ አማርኛ የመተርጎም፣ የፓተንት አዋጅን የማሻሻል ጅምር ስራዎች፣ በቅጅ መብት ስራዎች የሮያሊቲ አሰባሰብና አከፋፈል ሞዴል እንዲሁም የጋራ አስተዳደር ማህበር የአባላት የስነ-ምግባር ደንብ ማፅደቂያ መመሪያ ዝግጅት ስራዎች ፤ በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የፍትህ አካላት፣ ባለመብቶች፣ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ የስልጠናና የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ተጠቅሷል፡፡
በውይይት ወቅት የታዩ ክፍተቶችና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሰራተኞች የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተው በኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የጽ/ቤቱን የቀጣይ 10 ዓመት ስትራተጂያዊ ዕቅድ ማዘጋጀትና አፈጻጸምን በማሳደግ የጽ/ቤቱን ዓላማዎች ለማሳካት በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራም ተነግሯል፡፡