የአእምሯዊ ንብረት አሴት ልማት ዋና የሥራ ሂደት የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት
ታዋቂ የግብርና ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲሁም ሀገርበቀል እውቀቶችንና ዲዛይኖችን በፈጠራና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግና የተዋናዮችንና የአምራቾችን ተጠቃሚ በማድረግ ሂደት ውሰጥ ውጤታማና ከዘመኑ ጋር የተጣጣመ የአእምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋትና ሕጋዊ ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትም ከላይ የተጠቀሰውን መሠረታዊ ተልዕኮ ለመወጣት ይረዳው ዘንድ አዳዲስ አደረጃጀቶችን እያዋቀረና አሰራሮችን እየዘረጋ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት በአዲስ መልክ የተዋቀረው የአእምሯዊ ንብረት አሴት ልማት ዋና የሥራ ሂደት የተዋቀረባቸውን ጭብጦችና እያከናወናቸው የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራት በሚመለከት አጭር ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
- የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ጥበቃና ልማት
የኢትዮጵያ ባሕላዊ ሕክምና እውቀት የዳበረ የሰነድ፤የቴክኒክና የክህሎት መሰረት ካለቸው ሀገር በቀል የእውቀት ዘርፎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ወደ ሀገራችን ከመግባቱ በፊትም ሆነ ዘመናዊ ሕክምና በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት ለአብዛኛው የሀገራችን ሕብረተሰብ የጤና አገልግሎት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአእምሯዊ ንብረት እሳቤ ሲታይም ባሕላዊ ሕክምና እውቀት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍና ሲዳብር የመጣ የፈጠራና የሙከራ ድምር ውጤት ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ለአብዛኛዎቹ በአእምሯዊ ንብረት ዘዴዎች ለተጠበቁት ዘመናዊ መድሃኒቶች መነሻና መገኛ ሆኖ አገልግሏል፡፡
የሀገራችን ባሕላዊ ህክምና እውቀት በምርምርና ጥናት እንዳይዳብርና በስፋት ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደረጉት በርካታ ማሕበራዊና ሐይማኖታዊ ምክንያቶች ቢኖሩም በተደጋጋሚ የሚነገረውና በየመድረኩ በብሶት ጭምር የሚገለጸው እውቀቱን እየሰሩበት የሚገኙት ባሕላዊ ሀኪሞች የእውቀቱን ይዘት የሚመለከቱ መረጃዎችን በሚስጥር መያዛቸውና ሕይወታቸው ሲያልፍ ጭምር ይዘው መቀበራቸው ነዉ፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ባሕላዊ ሕክምና እውቀት በሚስጥር የሚያዝባቸው ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የባሕላዊ ሕክምና እውቀትን ሚስጥራዊነት ለመቀነስና እንደማንኛውም የቴክኖሎጂ መረጃ በቀለላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዱ ሌሎች የባሕልና አመለካከት ጉዳዮች ላይ መሥራቱ እንዳለ ሆኖ ከጽ/ቤታችን ተልዕኮ አንጻር ባሕላዊ እውቀቱን እየተገበሩ ለሚገኙት ባሕላዊ ሀኪሞችና ባለሙያዎች የአእምሯዊ ንብረት መብታቸውን ማስከበርና ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ ሰርተው መድሃኒቱና አገልግሎቱ የሚዳብርበትን አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ ሥራውን የሚመራ ቡድን ተደራጅቷል፡፡
በአእምሯዊ ንብረት አሴት ልማት ዋና የሥራ ሂደት ሥር ከተዋቀሩት ቡድኖች አንዱ የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ልማት ቡድን ሲሆን ቡደኑ የተዋቀረባቸው ዋና ዋና ተግባራት የሚከቱለት ናቸዉ፡፡
- ለሚመለከታቸው የምርምርና ተቋማትና የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ባለቤቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት
- ሞዴል የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ሽግግር ስምምነቶችን ማዘጋጀትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማገዝ
- ተመራማሪዎችንና የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ባለመብቶችን ማደራደርና ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን አሰራሮች መዘርጋት
- የባሕላዊ ሕክምና እውቀት ብሄራዊ መረጃ ቋት መመስረትና ለሚመለከታቸው አካላት ( ለምሳሌ ለፓተንት መርማሪዎች ) ተደራሽ ማድረግ
- የሀገር በቀል ዲዛይንና ቅርጻ ቅረጽ ልማት
ሐገርበቀል ዲዛይኖችና ቅርጻቅርጾች በተለያየ አካባቢ የሚኖሩና የተለያዩ ማሕበረሰቦችን እምነትና አመለካከት የሚያንጸባርቁ ባሕላዊ እሴት ከመሆናቸው በተጨማሪ የየሕብረተሰቦቹን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ፍላጎቶች ለማርካት ጥቅም ላይ የሚውሉ ወይም አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችንና የእደ ጥበብ ውጤቶችን ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ቁሳቁሶችንና የእደ ጥበብ ውጤቶች በእያንዳንዱ የስው ልጅ የሕይወት መስተጋብር ውስጥ ሊገለጡ የሚችሉ ቢሆንም በተለይ በሀገራችን በባሕላዊ ሙያነት ከሚታወቁት መካከል በሽመና ሥራ፤ በሸክላ ሥራ፤ በጣውላ ሥራ፤ በብረታብረት ሥራ ውስጥ የሚታዩት ፈጠራዎችና መሻሻሎች በአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ሊደገፉ የሚችሉ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ሐገርበቀል ዲዛይኖችና ቅርጻቅርጾች የጋራ ባሕሪያቸው በአብዛኛው በተወሰነና በትንሽ ቦታ የሚመረቱ እንዲሁም በሰው ጉልበት ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ማለት በፈጠራና ቴክኖሎጂ ቢደገፉ በገፍ ተመርተው ለገበያ መቅረብ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዲዛይኖችና ቅርጻቅርጾች ላይ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር ቢደረግባቸው በምርት ሂደት ላይ የሚታዩ ቴክኒካዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ ፈጠራዎችን ለማመንጨት እንደመነሻ ሆነው ማገልገላቸው እንዳለ ሆኖ በዲዛይኖችና ቅርጻቅርጾች ላይ የሚንጸባረቁት ባሕላዊ እሴቶችና ትውፊቶች በዘርፉ ለሚመረቱ ምርቶችና ለሚሰጡ አገልግሎቶች ተፈላጊነትንና የዋጋ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ዋነኛ ስትራቴጂ ሆኖ ሊሠራባቸው ይችላል፡፡ የሀገር በቀል ዲዛይኖችና ቅርጻቅርጾችን ለማልማትና ለማሻሻል በተለያዩ ተቋማት እና አደረጃጀቶች መከናወን የሚገባቸው በርካታ ተግባራት እንዳሉ ሆነው በአእምሯዊ ንብረት አሳቤ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት ለመደገፍ በአእምሯዊ ንብረት አሴት ልማት ዋና የሥራ ሂደት ከሚያከናወናቸው ተግባራት መካከል፡-
- ለእደ ጥበብና ቅርጻ ቅረጽ ባለሙያዎችና ማሕበራት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት
- ለእደ ጥበብና ቅርጻ ቅረጽ ባለሙያዎች ከሌሎች አምራቾችና ባለሃብቶች ጋር የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት
- ከአስፈጻሚ አካላት ጋር መስራትና የአሠራር ሥርኣት መዘርጋት
- ባለልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶች ጥበቃና ልማት
ባለልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶችንና ተያያዥ አገልግሎቶችን የገበያ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና አምራቾችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ምርቶቹንና ተያያዥ አገልግሎቶችን በምቹ የአእምሯዊ ንብረት ዘዴ ( ብራንድ ) ማስጠበቅ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትም በዚህ ረገድ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የተወሰኑ ታዋቂ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውሰጥ እና በውጪ ሀገራት እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡ በሀገር ውሰጥ የተደረገው ጥበቃ የንግድ ምልክት አዋጅ (501/1998) መሠረት በማድረግ የተደረገ የወል ንግድ ምልክት ምዝገባ ሲሆን አብዛኛዎቹ ምርቶች በጋራ የሚመረቱ አካባቢያዊ ምርቶች ናቸው፡፡ በዚህ አግባብ በወል ንግድ ምልክት ከተመዘገቡት የግብርና ምርቶችና የእደ ጥበብ ውጤቶች መካከል የጅሩ ሠንጋ፤ የደብረ ሲና ቆሎ፤የመንዝ በግ፤ የወሎ ጋቢ፤የደሴ ሣፋ፤ የምንጃር ጤፍ፤የአረርቲ ሽምብራ፤ ይገኙበታል፡፡ በውጭ ሀገራት ከተመዘገቡት ምርቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ሦስቱ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ማለትም ሐረር፤ ይርጋ ጨፌና ሲዳሞ የቡና ስሞች ሲሆኑ በዋና ዋና የሀገራችን የቡና ገበያ መዳረሻ ሀገራት በንግድ ምልክት ተመዝግበው ሕጋዊ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡
የግብርና ምርቶችን እና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማዝመዝገብና የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳግ ሚከናወኑት ሥራዎች በቅንጅት የሚሰሩና በአንድ ተቋም ብቻ የሚከናወኑ አይደሉም፡፡ በዚሁ መሠረት ባለልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶች ጥበቃና ልማት ቡድን ከሚያከናውናው ተግባራት መካከል
- ሊመዘገቡ ሚችሉ ታዋቂ የግብርና ምርቶችን መለየትና ማስጠናት
- የአምራቾችን እና አስፈጻሚ አካላትን አቅም መገንባት
- የተመዘገቡ የንግድ ምልክቶችና የወል ንግድ ምልክቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚወሉበትን ሥልት መቀየስና
- የተመዘገቡ ብራንዶችን ሕጋዊ ተፈጻሚነት መደገፍ የሚሉት ይገኙበታል