የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ለቤተክርስቲያኗ ቤተክህነት የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊዎችና ልዩ ኮሚቴ አባላት በአእምሯዊ ንብረት ጽንስ ሃሳብና የጥበቃ ስርዓት ዙሪያ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በቤተክህነቱ ቅፅር ግቢ ሥልጠና ሰጠ፡፡
የቤተክህነቱ ልዩ ኮሚቴ ተወካዮች ቤተክርስቲያኗ ያሏትን የአእምሯዊ ንብረት ሃብቶች ለማስመዝገብና ለማስጠበቅ ከጽ/ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ሥልጠናው የተዘጋጀ ሲሆን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ፣ የማህበረሰብ እውቀቶችና የትውፊት ሃብቶች ጥበቃ እንዲሁም የፓተንት መብት ጥበቃ ሥርዓቶችን አስመልክቶ በባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ቤተክርስቲያኗ ያሏትን ዘርፈ ብዙ ሃብቶች በመደበኛ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ህጎች እና በሌሎች አግባቦች ማስጠበቅ በምትችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡