በአእምሯዊ ንብረት መብቶች በተለይ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ 410/96 እና በማሻሻያው አዋጅ 872/07 ምንነት፣ የአዋጆቹ አተገባበር፣ የመብቶች ተፈጻሚነት፣ ጥበቃ የሚያስገኙ ስራዎችን እንዲሁም የምዝገባ ጠቀሜታን አስመልክቶ በሀድያ ዞን ከፍትህ አካላት፣ ከባህልና ቱሪዝም ከተውጣጡ ባለሙያዎች፣ ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች፣ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ መምህራን አንዲሁም ባለመብቶች በሆሳዕና ከተማ ጥር 19/2014 ዓ.ም ውይይት ተካሄደ፡፡የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሐዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ዳኜ ግርማ በመክፈቻ ንግግራቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ኃላፊነትና ተግባር እንዲሁም በቅርንጫፉ የተከናወኑ ተግባራትን ገልጸዋል፡፡ የአእምሯዊ ንብረት በህበረተሰቡ ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ ተከታታይ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማመቻቸት እንደሚያሻ አክለው ገልጸዋል፡፡የቅጅ መብት የሚያስገኙ ስራዎች ወጥና ግዙፍነት ካገኙ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚሰጣቸው ለመወያያ በቀረቡ ጽሁፎች ተብራርቷል፡፡ የቅጅ መብትን የሚያስገኙ ስራዎችን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አለማስመዝገብ መብት የማያሳጣ ቢሆንም በስነ-ጽሁፍ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በስነ-ጥበብ፣ በኮምፒተር ፕሮግራም እና በመሰል ዘርፎች የሚገኙ የፈጠራ ስራዎችን ማስመዝገብ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተብራርቷል፡፡ከጠቀሜታዎቹም የተወሰኑት የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ህጋዊ የንብረት ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የመብት ዝውውርን ለመፈጸም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መሆናቸው በመወያያ ጽሁፎቹ ተመላክተዋል፡፡የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ግንዛቤ በስፋት መፈጠር እንደሚገባና ዘርፉ ሊያስገኝ የሚገባውን ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረውን ፋይዳ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ጥያቄና አስተያየት ከተሳታፊዎች ቀርቦ በጽሁፍ አቅራቢዎች ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡