የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን “IP and Sport: Ready, Set, Innovate” / “አእምሯዊ ንብረትና ስፖርት፡ መዘጋጀት፣ መጀመር፣ መፍጠር” በሚል መሪ ቃል ቅዳሜ ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም በሀገራችን የመጀመሪያ በሆነውና በቅርቡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተመረቀው አዲስ ስፖርት ፓርክ በስፖርታዊ ውድድር እና በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡

በበዓሉ መክፈቻ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ወልዱ ይመሰል በስፖርት ዓለም ውስጥ የሚከሰቱ የተወዳዳሪዎች የግልና የጋራ ፈጠራዎች፣ ንድፎች፣ ብራንዶችና የመልካም ዝና ታሪኮችን ለመጠበቅና ሀገራትን ጭምር ለማስተዋወቅ የአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ስርዓት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስተር ዲኤታ ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) እንደገለጹት “አእምሯዊ ንብረት ቀንን ስናከብር እንዘጋጅ፣ እንጀምር፣ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን በስፓርት ዓለም ውስጥ የሚፈጠሩ ክስተቶችን፣ ንድፎችን፣ ብራንዶችን ለማስጠበቅ እና ተጠቃሚ ለመሆን አእምሯዊ ንብረት ቁልፍ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
በፓናል ውይይቱም ያደጉ ሀገራት በመብት ጥበቃ ስርዓት በመዘርጋታቸው ከአእምሯዊ ንብረት በከፍተኛ ደረጃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸው፣ አእምሯዊ ንብረት በስፓርት ውስጥ ያለው ፋይዳ፣ የሀገር ገፅታን ለመገንባት የሚጫወተው ሚና በስፓርቱ ኢንድስትሪ ውስጥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች አቅም ግንባታ ስልጠና የግንዛቤ እና ተደራሽነት፣ ከዘርፋ ጋር በተያያዘ በምርምር እና በዩንቨርሲቲዎች ያለው እንቅስቃሴ ሊመዘገብ እና ጥበቃ ሊያገኙ የሚገባቸው የስፓርት ውጤቶች እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ሃሳቦች ላይ የአውደ ጥናት ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስመ ጥር የሆኑ አትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኗ መጠን ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አለመሆኗን ጠቁመው በስፓርቱ ዘርፍ ያሉትን የአእምሯዊ ንብረት ውጤቶችን ወደ ገበያ ማውጣት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ እንደገለፁት የተለያዩ ዓለም አቀፍ አትሌቶችን በመጠቀም ሀገርን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመው ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።