
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እያከናወነ ስላለው ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 18/2018ዓ.ም አዜማን ሆቴል የውይይት መድረክ አካሄደ።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይምስል እንደገለፁት አእምሯዊ ንብረት ለአንድ ሀገር ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ እየሆነ መምጣቱን ገልፀው ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራባቸው ስለሚገኙት የህግ ማሻሻያዎች፣ የዲጅታል አገልግሎት ፣የሰው ሃብት ልማት፣አገልግሎት ማዘመን እንዲሁም ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቋሙው ተቋሙ ከአእምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረመ ሲሆን ከዘርፍም የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአደጉ ሀገራት የአእምሯዊ ንብረት ማመልከቻ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ እያጋጠሙ ያሉትን የፓሊሲ፣ የህግ የዲጅታል የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የመረጃ ቋት ግንባታን፣ አቅም ግንባታ ፣ የሚዲያ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል ።
ዋና ዋና አእምሯዊ ንብረትን የሚያስተዳድሩ ህጎች ዓለም አቀፍ አእምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) እና አለም አቀፍ የንግድ ድርጅት (WTO) እንዲሁም ተቋሙ እያከናወነ ያለውን የንግድ ምልክት የፓተንት የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች የማሻሻያ አዋጅ ፣ የመልክዓ ምድራዊ አመላካች የህግ ማዕቀፍ በተለይም አገራችን ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት የቡና ምርት ከዓለም አቀፍ ገበያ አንፃር ምን እንደሚመስል የማህበረሰብ እውቀት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ወርቁ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ ተቋሙ 120 የሚደርሱ አገልግሎት መለየቱን አያይዘው ገልፀዋል።
የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር እንዳለው ሞሲሳ ውይይቱን የመሩ ሲሆን ተሳታፊዎች በዋና ዋና የአእምሯዊ ንብረት ነባር እና አዳዲስ ህጎች እንዲሁም ተቋሙ ከየት ተነስቶ ወዴት መድረስ እንደሚሻ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ተቋሙ የሪፍርም ሥራዎችን ቀደም ብሎ የጀመረ መሆኑን አመላክተው እንደሀገር የመጣው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ሥራም የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም የበለጠ እንደሚያጠናክር አንስተዋል፡፡ ከውይይት መድረኩም የተለያዩ ግብዓቶች በመሰብሰብ ወደ ተግባር ለማውረድ የታለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የተቋሙ ወኪሎች፣ የፍትህ አካላት፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም ጉዳዮ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል።

ከተሳታፊዎችም ቅንጅታዊ አሰራር፣ የሪፎርሙ የትግበራ ሁኔታ፣ የሀገር በቀል ፈጠራዎች ማጠናከር እና ከዘርፍ ተጠቃሚነት አንፃር መከናወን ያለባቸው ተግባራት፣ ከተደራሽ እና ከግንዛቤ አንፃር፣ የመረጃ ቋት ማዕከል መገንባት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዋፆኦ፣ አለምአቀፍ ስምምነቶች እና የሚኖራቸው ፋይዳ፣ አእምራዊ ንብረትን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከቤቱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል።