የኢትዮጵያን ባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ብራንድ ለማስመዝገብ የተተገበረው ፕሮጀክት ስኬቶችና ድክመቶች

በታደሰ ወርቁ

ባለልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶችንና ተያያዥ አገልግሎቶችን የገበያ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና አምራቾችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ምርቶቹንና ተያያዥ አገልግሎቶችን በምቹ የአእምሯዊ ንብረት ዘዴ (ብራንድ) ማስጠበቅ የተለመደ አሠራር ነው፡፡በተለይ የግብርና ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲሁም ሀገር በቀል እውቀቶችንና ዲዛይኖችን በፈጠራና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግና የተዋናዮችንና የአምራቾችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለውን ፋይዳ በመረዳት በቡና ብራንድ ምዝገባ ላይ ፕሮጀክት ተዘጋጅቷል፡፡

ቡና በአብዛኛዎቹ የሀገራችን አካባቢዎች የሚመረትና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ተደርጎ የሚጠቀስ የግብርና ምርት ነው፡፡በበርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው በሀገራችን በቡና ዘርፍ የሚተዳደረው የሰው ሃይል ብዛት እና ዘርፉ ለብሔራዊ ኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦና ድርሻ ከሌሎች የሀገራችን የሥራ መስኮች ደርሻ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በጣም የጎላ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗና በርካታ የቡና ዝርያዎች መኖራቸው እንዲሁም ሰፊ ትንታኔና ትርጉም ሊሰጥባቸው የሚችሉ ባሕላዊ እውቀቶችና የቡና አፈላል ሥነሥርዓቶች መኖር ዘርፉ አሁንም በሰፊው ሊሰራበት የሚችል ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እምቅ አቅም እንዳለው ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ይህ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተለያዩ መድረኮች ብዙ ቢዘመርለትም በተለይ ቡና በማምረት የሚተዳደረውና ኑሮው በቡና ላይ በተመሰረተው አርሶአደር ሕይወት ላይ እየመጣ ያለው ለውጥ የሚጠበቀውን ያህል ሆኖ አልተገኘም፡፡ የዚህ ችግር ዋናኛ ምክንያት ደግሞ ከንግድ ሥርዓቱ ኢፍትሃዊነት የሚመነጭና በቡና ግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የቡና አምራቹ አርሶ አደር ያለው የመደራደር አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ገበያው የሰጠውን ዋጋ ብቻ እንዲቀበል መገደዱ ነው፡፡

በበርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው አንድ  ኪሎ ቡናን የቡናው አምራች አርሶ አደር ሲሸጠው የሚያገኘው  የተጣራ ዋጋና ያንኑ ተመሳሳይ መጠንና ጥራት ያለውን ቡና የታወቀ ኩባንያ እሴት ጨምሮበት ለተጠቃሚው ሲሸጠው  በሚያገኘው ዋጋ መካከል ሠፊ የዋጋ ልዩነት ይታያል፡፡ እርግጥ ነው በቡናው ላይ እሴት የመጨመሩ ሂደትና ምርቱን በተመቻቸ አውድ ውሰጥ ለተጠቃሚ ማቅረቡ ሥራ የዋጋ ልዩነት መፍጠሩ የሚጠበቅና ትክክለኛ አሠራር ነዉ፡፡ ነገር ግን ይህ የዋጋ ልዩነት በአሳማኝ የእሴት ጭማሪ ምክንያቶች ብቻ የሚፈጠር ልዩነት እንዳልሆነ የሚገባንና የሚያስቆጨን በቡና ላይ እሴት ሚጨምርባቸው አንዳንድ ተግባራት ቀላል መሆናቸውን ስንመለከት ፤ አብዛኛዎቹ የሀገራችን ቡና ላኪዎች  ቡናውን ሁልጊዜ በጥሬው  በጆንያ እያሸጉ በመላክና እንደማንኛውም የግብርና ምርት ዋጋው በገበያው በራሱ ብቻ እንዲወሰን ሲያደርጉ  እንዲሁም ቡናችን ያለውን ዓለማቀፋዊ ዝናና ተዋቂነት ( ብራንድ )  በአግባቡ ተረድተን የቡናውን የገበያ ተወዳዳሪነት በሚያሳድግ መልክ ብዙም ያልተሰራበት  መሆኑን ስንረዳ ነው፡፡ 

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ይህንን ኢፍትሃዊ የንግድ አሰራር ለማስተካከልና  የቡና አምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ይረዳል ተብሎ የታመነበት የኢትዮጵያ ታዋቂ የቡና ስሞች ብራንዲንግ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ተተግብሯል፡፡

የፕሮጅቱ ዓላማ ምን ነበር?

 በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አዘውትሮ ሲገለጽ እንደሚታየው የቡና ዋጋ ዝቅተኛነትና በዓለም ገበያ ላይ የሚከሰተው የዋጋ መዋዠቅ የሚያስከትለው ተጽእኖ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት ቡናን በማምረት ብቻ የሚተዳደሩት ድሃ አርሶ አአደሮች ናቸው፡፡ በዚሁ መነሻነት የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ መዋዠቅ ችግር መሠረታዊ መንስጼ ምንድነው ምንስ ሊደረግ ይገባል የሚለውን ጭብጥ በጥናት ርዕስነት በመያዝ Light years IP ተብሎ የሚታወቀው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰፊ ጥናት አድርጎበታል፡፡ 

በጥናቱ ውጤት መሠረት የቡና አምራቹ አርሶ አደር በገበያ መዋዠቁ ምክንያት ለበርካታ ማሕበራዊና አኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ጠቅሶ በተለይ በጉልህ ከተቀመጡት ችግሮች መካከል

  1. ቡና በማምረት የሚተዳደሩት አርሶ አደሮች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንኳን ማሟላት አለመቻላው፤
  2. ቡና ያመርቱበት የነበረውን መሬት ቡናውን በመቁረጥ ሌሎች በቀላሉ ገንዘብ የሚያስገኙ ምርቶችን (ለምሳሌ ጫት) መተካትና ማምረት፤
  3. ሠፊ አማራጭ የነበራቸው የቡና ዝርያዎች መመናመን ወይም የዝርያዎች ተለያይነት እየቀነሰ መምጣቱና በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ አሉታዊ ለውጥ መታየቱ የሚሉት መሠረታዊ ችግሮች ይገኙበታል፡፡

እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት መከናወን የሚገባቸው በርካታ የምርምርና የንግድ  ተግባራትና የመፍትሄ  ማራጮች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ቡና ካለው ዓለማቀፍ ተፈላጊነትና ዝና  መሠረት የብራንድ ጥበቃ ቢደረግለት (በንግድ ምልክት ቢመዘገብ) እና ዘመናዊ የግብይት ሥርኣት ቢዘረጋለት የቡና አምራቾችን በገበያ የመደራደር አቅም ይጨምራል የሚለውን የጥናቱን መፍትሄ ሃሳብ በመውሰድ Ethiopian Coffee Trademarking & Licensing  Initiative   የሚል ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች እነማን ነበሩ?

 የፕሮጀክቱ ሃሳብ በዋነኛነት በተወሰኑ ግለሰቦች ግንባር ቀደም መሪነት የተከናወነ ቢሆንም በዋነኛነት Light years IP የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በቡናው ግብይት ላይ ያሉ ኋላ ቀር አሠራሮችንና እየተከሰቱ የነበሩ ችግሮችን  በጥልቀት በማጥናት የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረቡ ተጠቃሽ ባለውለታ ተደርጎ ሊታይ ይገባል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ  በአሜሪካ ሀገር የሚገኘው Arnold & Porter  ተብሎ የሚታወቀው የህግ ድርጅት የንግድ ምልክቶቹን በማስመዝገቡና እስከ ቅርብ ጊዚያት ድረስ ንግድ ምልክቶቹን በማሳደስ ነጻ የሙያ አገልግሎት ( Pro bono legal services ) የሰጠ የፕሮጀክቱ ተሳታፊ ድርጅት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በገንዘብ የደገፈው UK Department for International Development የተባለው የእንግሊዝ የልማት ድርጅት ነበር፡፡  የሀገር ውሰጥ የፕሮጀክት ተሳታፊዎችን በሚመለከት ከግብርና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ፤ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ከአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትና ከዋና ዋና ቡና ላኪዎችና አምራቾች ማሕበራት የተውጣጣ  Stakeholders Committee የተሳተፉበት ሲሆን አብዛኛዎቹን ቴክኒካዊ ጉዳዮች የተወሰኑት በዚህ አካል አማካኝነት ነው፡፡

የተመዘገቡት የታዋቂ ቡና ስሞች ሕጋዊ አጠቃቀም እንዴት ይተገበራል?

የተመዘገቡትን የቡና ንግድ ምልክቶችን በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋልና በፕሮጀክቱ የተነደፈው መሠረታዊ  የቡና ዋጋ መዋዠቅና የዋጋው መቀነስ  ችግርን ለመፍታት የተነደፈውን ሥልት ስንመለከት በወቅቱ ሥራውን የሚመሩት ተቋማትና የቴክኒክ አደረጃጀቶች ቁርጠኝነትና ሙያዊ ብቃታቸውን  በግልጽ ያሳያል፡፡ የታዋቂ ቡና ስሞች በውጭ ሀገራት የማስመዘገቡ ሥራ እንደተጠናቀቀ ቡናዎቹን ለመሸጥ የሚፈልጉ ላኪዎችና ገዥዎች ንግድ ምልክቱን የሚጠቀሙበትን አግባብ በተመለከተ በርካታ አማራጮች ጥቅምና ጉዳታቸው ከተተነተነ እና ከተመዘነ በኋላ ወጥ የሆነ የውል ሥምምነት ተዘጋጅቶ የኢትዮጵያን ቡና መነገድ የሚፈልጉ ኩባንያዎች ሁሉ ፈርመው ንግድ ምልክቱን እንዲጠቀሙ ተወሰነ፡፡ በዚሁ መሠረት ወደ  90 የሚጠጉ ዓለማቀፍ የቡና ነጋዴዎችና ኩባንያዎች እንዲሁም ወደ 60 የሚጠጉ የሀገር ውሰጥ ቡና ላኪዎችና ማሕበራት  በየ አምስት ዓመት የሚታደስ የውል ስምምነት ፈርመዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ ስምምነቱን ፈረሙት ኩባንያዎች ከገቧቸው ግዴታዎች መካከል በየሀገራቸው የኢትዮጵያን ቡና እንዲያስተዋውቁና እንዲሁም በየሀገራቱ  የሚከሰቱ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለኢትዮጵያ ሪፖርት እንዲያደርጉ ነበር፡፡ የዚህ ተግባር ዓላማም ኩባንያዎቹ ካላቸው ዓለማቀፍ ተደራሽነት አንጻር በቡናዎቹ ላይ የሚሰራው ማስተዋወቅና የሕጋዊ ተፈጻሚነት መጠናከር በድምር ውጤት ሲታይ የቡናን ዋጋ ስለሚያሳድገው በሂደት አምራቹን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት ነበር፡፡  በሌላ መልኩ የንግድ ምልክቱን ለመጠቀም ውል የፈረሙት ቡና ላኪዎችና ቡና ገዥ ኩባንያዎች የሚፈጥሩት የውል ፈራሚዎች ጥምረት ( Network of Licensed Exporters and Buyers ) መጠናከር ቡናው በተወሰነ ሰንሰለት ብቻ የሚሸጥበትን አሰራር ስለሚፈጥር  የቡናውን ዋጋ በድርድርና በፍትሃዊ መንገድ ለመወሰን ይረዳል ተብሎ የታመነበት ውሳኔ ነበር፡፡  ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮችና ሌሎችም የውል ስምምነቱ  የያዛቸው ዘመናዊ የንግድ ሥራ አሠራሮችና እሳቤዎች በተሟላ መንገድ ተተርጉመው ቢሆን ኖሮ በቡና ግብይት ሥርዓቱ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በገሃዱ የሆነውና ሲተገበር የታየው የዚህ ተቃራኒ ነው ፡፡ ለአብነት ያህል በውል ስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ቡናውን ወደ ውጭ ስትልክ የውል ስምምነቱን ለፈረሙት ብቻ መሸጥ ሲገባት የውል ፈራሚዎች ጥምረትን ( Network of Licensed Exporters and Buyers ) እንዳይጠናከር በሚያደርግ መልኩ ቡና ገዥ ነኝ ብሎ ለሚመጣው ሁሉ ቡናው መሸጥ ቀጠለ፡፡

ይህንን ተከትሎ ውል ሳይፈርሙ የኢትዮጵያን ቡና የሚነግዱት እና ውሉን ፈርመውና ግዴታቸውን አክብረው የኢትዮጵያን ቡና በሚነግዱት ኩባንያዎች መካከል ልዩነቱ ጠፋ፡፡ ውሉ የፈረሙት ኩባንያዎችም ቡናው ለሁሉም የሚሸጥ ከሆነ ውሉን መፈረማችንንና ግዴታ ውስጥ መግባታችን አግባብ አይደለም ብለው ተቃውሞ አቀረቡ፡፡ በዚህም የተነሳ በየ አምስት ዓመቱ መታደስ የነበረበት የውል ስምምነት በአንድም ኩባንያ ሳይታደስ በዚያው ተረስቶ ቀረ፡፡

  የፕሮጀክቱ ሥኬቶች ተደርገው ሊቆጠሩ የሚችሉት ጉዳዮች ምንድ ናቸው?

ፕሮጀክቱ ያመጣውን አዎንታዊ ለውጥ ለመገምገምና በተጨባጭ ለመግለጽ በመሬት ላይ ወርዶ ወቅታዊ ጥናት ማካሄድ የሚያስፈልግ ቢሆንም ከዚህ ጽሁፍ አላማ አንጻር ዶኩመንቶችንና ተያያዥ መረጃዎችን በመጠቀም የተወሰኑ ስኬቶችን እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

1ኛ. ሦስቱ የሀገራችን የቡና ስሞች ማለትም ሐረር፤ ይርጋቸፌና ሲዳሞ ወደ 30 በሚጠጉ ሀገራት በንግድ ምልክትነት መመዝገባቸውና በስሞቹ ላይ ያለው ሕጋዊ መብት መጠበቁ፤

2ኛ. የኢትጵያን ታዋቂ ቡናዎች ያለከልካይ ሲጠቀሙ ከነበሩ ኩባንዎች (በተለይ ከ STAR BUCKS) ጋር የነበረው ክርከር በኢትጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁና ያንን ተከትሎ የመጣው የዲፕሎማሲና የቡና ተጠቃሚዎች ግንዛቤ ማደጉ፤

3ኛ. ምንም እንኳን በሂደት ችግር ገጥሞት የታለመለትን ውጤት ባያመጣም ወደ 90 የሚጠጉ ዓለማቀፍ የቡና ነጋዴዎችና ኩባንያዎች እንዲሁም ወደ 60 የሚጠጉ የሀገር ውሰጥ ቡና ላኪዎችና ማሕበራት የተመዘገቡትን የንግድ ምልክቶች በውል ስምምነት መሠረት ፈርመው ለመጠቀም ግዴታ መግባታቸውና ውል መፈረማቸው እንዲሁም ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የቡና ተዋናይ ወደ ሕጋዊ አሠራር ማምጣትና የሀገሪቱን ፍላጎት እንዲቀበሉ ማድረግ ፋይዳው ቀላል አልነበረም ፡፡

የፕሮጀክቱ ውድቀቶችና ድክመቶች ተደርገው ሊቆጠሩ የሚችሉት ጉዳዮች ምንድናቸው?

ሃብትና እውቀት አቀናጅቶ ፕሮጀክት በመቅረጽና በመተግበር የአንድን ሀገር ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት መሥራት የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ነገር ግን በሀገራችን የተተገበሩት አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በባሕሪያቸው በጊዜ የተገደቡና ለወቅቱ ብቻ የተመደቡ ተዋናዮች የሚሳተፉባቸው በመሆናቸውና ኮሚቴዎቹ ሲፈርሱና ባለሙያዎቹ ወደየተቋሞቻቸው ሲመለሱ የፕሮጀክቱን ውጤቶች የሚያስቀጥል እና በተጠያቂነት የሚሰራ አካል ይጠፋል፡፡

በእርግጥ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው በጉዳዩ ላይ የሚሰራ አካል ይጠፋል ሲባል የፕሮጀክቱ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት በፕሮጀክቱ አማካኝነት ሲከናወኑ በነበሩ ሃሳቦች ዙሪያ ሥራ አይሰሩም ለማለት ሳይሆን የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶና በፕሮጀክቱ የተገኙ ውጤቶችን በሚያጎለበትና በሚያሻሽል መልኩ ሥራው አለመሰራቱን ለመግለጽ ነው፡፡

 Ethiopian Coffee Trademarking&Licensing Initiative በሚል ተዘጋጅቶ የተተገበረው ፕሮጀክትም የታዩበት ክፍተቶችና ጉድለቶች ከላይ ከተገለጸው ችግር ጋር በቀጥታ የተገናኘ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ፕሮጀክቱ በቡና ላይ የሚሰሩ በርካታ ተቋማት የተሳተፉበት ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን የትግበራ ዘመኑ ሲያልቅ የፕሮጀክቱን ውጤቶች ማን ያስቀጥላቸው? የትኛው ተቋም ምን ድርሻ ይኑረው; ወይስ የፕሮጀክቱን ሥራ በዘላቀነት ሊሰራ የሚችል ሌላ አደረጃጀት ሊፈጠር ይገባል? የሚሉትና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የፕሮጀክቱ ውድቀቶች ማሳያ ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የዚህ ችግር ሌላው ማሳያ ደግሞ ንግድ ምልክቶቹ በተመዘገቡባቸው ሀገራት የእድሳት ጊዜያቸውን ጠብቆ የሚያሳድሳቸው ማነው ንግድ ምልክቶቹን በሕገ ወጥ መንገድ ሌሎች ቢጠቀሙባቸውስ የሚከታተለው ማነው የንግድ ምልክቱን ለመጠቀም የተፈረሙት የውል ስምምነት አሰራር እንዴት ይጀመር ማን ይስራው ወዘተ. በርካታ መላሹ የጠፋበት ጥያቄ …..

ምን ቢደረግ ይበጃል?

በጥቅሉ ሲታይ የፕሮጀክቱ ዓላማ በሚጠበቀው መጠን ያልተሳካውና ይፈታሉ የተባሉት ችግሮች ሳይፈቱ የቀሩት በሀገሪቱ የቡና ግብይት ሥርኣት ውሰጥ የሚስተዋለው ኋላቀር አሰራር እና ሕገወጥ ተግባራት ተመጋግበው የሚከናወኑበት በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ የቡናው ዘርፍ የሚመራበት አደረጃጀት ዘመናዊ የንግድ አሰራር በሚመራበት ስልት አለመደራጀቱ፤  እንዲሁም በግሉ ዘርፍ እና በመንግስታዊ መዋቅሩ መካከል ያለው መስተጋብር የተናበበ ባለመሆኑ በስኬትነት የተመዘገቡትን የፕሮጀክቱን ውጤቶች በዘላቂነት ለማስቀጠል አላስቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ሥራውን በተሟላ ሐላፊነት ወስዶ የሚሰራ ተቋም የሌለ ሲሆን ፤ በቡና ላይ የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ቢኖሩም የፕሮጀክቱን ውጤቶች ለማስቀጠል በሚያስችልበት  አግባብ- ለምሳሌ ያህል የንግድ ምልክቶቹን ማሳደስ፤ ቀድሞ ውል ፈርመው የነበሩ ኩባንዎችንም ይሁን አዳዲስ የንግድ ምልክት ተከራይ ኩባንያዎችን  በማምጣትና ማስፈረም እንዲሁም ሕጋዊ ተፈጻሚነትን በማረጋገጥ ዙሪያ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም፡፡

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታትና በፕሮጀክቱ የተገኙትን ስኬቶች ለማስቀጠልና ፕሮጀክቱ ሲዘጋጅ መነሻ የነበሩ መሠረታዊ የቡና አምራቾችን ችግሮች ለመፍታት ይቻል ዘንድ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች መተግበር ይገባል፡፡

  1. የተመዘገቡትን የቡና ንግድ ምልክቶች (ብራንዶች) በባለቤትነት ወስዶ የሚያስተዳድር አደረጃጀት መፍጠርና የእድሳት ጊዜያቸው የደረሰ ንግድ ምልክቶችን በየተመዘገቡበት ሀገር ማሳደስ፡፡
  2. የሀገሪቱን የቡና ግብይት እንደማንኛውም የግብርና ምርት ዋጋው በገበያ ከሚወሰን ይልቅ የብራንድ አሰራሩን መተግበርና የቡና አምራቹን ተደራድሮ የመሸጥ አቅም ማጎልበት
  3. የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይ የኢኮኖሚ ዘርፉ የኢትዮጵያን ቡናዎች የሚሸጡ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች የንግድ ምልክት አጠቃቀም ውል እንዲፈርሙ ማግባባትና ማሰፈረም
  4. በሀገር ውሰጥ የሚገኙ የቡና አምራቾችና ላኪዎች የተመዘገቡትን የቡና ንግድ ምልክቶች የሚጠቀቡበትን ሕጋዊ አሠራር በዘርጋት
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS