የአእምሯዊ ንብረቶችን በማስየዝ ብድር ማግኘት ይቻል ይሆን? ፈጠራየስ ስንት ያወጣ ይሆን?
በፍሬው ተገኝ
የአእምሯዊ ንብረቶች ሊታዩ (ሊዳሰሱ) የማይችሉ በመሆናቸው እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማስገኘት ደግሞ የተለያዩ ቁሳዊ ሃብቶችን እና ሌሎች ግብአቶችን የሚጠቀሙ በመሆናቸው በመጨረሻ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ውስጥ ምን ያህሉ በአእምሯዊ ንብረት መብቶች ምክንያት እንዲሁም ምን ያህሉ በተጠቀሟቸው ቁሳዊ ሃብቶችና ግብዓቶች የመነጨ እንደሆነ ለመየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም አብዛኛውን የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ይህን ያህል ዋጋ ያወጣሉ ብሎ በቀላሉ ለመተመን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ባለሙያዎች የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ዋጋ ከሌሎች ቁሳዊ ንብረቶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የትመና ንድፈ ሃሳቦችንና ዘዴዎችን መሰረት በማድረግ ለአእምሯዊ ንብረት መብቶች በሚስማማ መልኩ በማስተካከል የአእምሯዊ ንብረት ዋጋን መተመን ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የአእምሯዊ ንብረት የዋጋ ትመናን በሶስት ዓበይት መንገዶች መተግበር ይቻላል፡፡

እነሱም፡- 1. ከወጪ አንፃር (Cost Method)
2. ከገበያ ዋጋ አንፃር (Market Methods)
3. ከገቢ መጠን አንፃር (Income method) ናቸው፡፡
እነዚህ የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ ትመና ዘዴዎች ደግሞ በውስጣቸው ሌሎች ንኡስ የትመና ዘዴዎችን የሚያካትቱ ሲሆን ከዚህ በታች አጠር ባለመልኩ ለማየት እንሞክራለን፡
- ከወጪ አንጻር (Cost Method)
ይህ የአእምሯዊ ንብረት ትመና መንገድ የአእምሯዊ ንብረትን (ምሳሌ፤ ቴክኖሎጂን) ዋጋ የመተመኛ መንገድ፣ነው፡፡ የአእምሯዊ ንብረቱ ባለቤት ለመሆን ወይም ንብረቱን ለማፍራት የወጣውን ወጪ መሠረት በማድረግ የሚሰላ የትመና ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ፈጠራን (የአእምሯዊ ንብረትን) ከወጪ አንፃር በመተመን መንገድ ውስጥ ሁለት ስልቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
1.1 ‹‹የታሪካዊ ወጪ መንገድ›› (Historical cost approach) አንዱ ሲሆን፤ ይህም የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ ለመተመን የአእምሯዊ ንብረቱን (ቴክኖሎጂውን) ለመፍጠር፣ ለማምረት (ለማበልፀግ) ከመጀመሪያው ጀምሮ በምርምርና መሰል ተግባራት የወጣውን ወጪ በሙሉ በመደመር የአእምሯዊ ንብረቱ (ቴክኖሎጂው) ዋጋ ነው ብሎ ግምት በመውሰድ የሚዘጋጅ የመተመኛ መንገድ ነው።
1.2 ‘’ለመተካት የወጣ ወጪ መንገድ’’ (Replacement Cost Approach) ሌላኛው መንገድ ሲሆን፤ እርሱም የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ የሚያሰላው ሊተመን የታሰበውን የአእምሯዊ ንብረት ወደፊት እንደ አዲስ እንፍጠረው፣እንግዛው (እናበልፅገው) ብለን በምናባችን በማሰብና ወደፊት የሚያስፈልገውን ወጪ ከግምት በማስገባት የአእምሯዊ ንብረትን የመተመኛ መንገድ ነው፡፡
2. ከገበያ ዋጋ አንፃር መተመን (Market Methods)
ከገበያ ዋጋ አንፃር የመተመን ዘዴ ተመሳሳይ የሆኑ የአእምሯዊ ንብረቶች ከዚህ በፊት በገበያ ላይ በምን ያህል ዋጋ እንደተሸጡና የእነዚህንም ግብይቶች ዋጋ አሁን ላይ ለመተመን የተፈለገውን የአእምሯዊ ንብረት እንደ መነሻ በመውሰድ የሚደረግ የትመና ዓይነት ነው፡፡ ተነፃፃሪ (ተመሳሳይ) የሆኑ የአእምሯዊ ንብረቶች (ቴክኖሎጂዎች) በገበያ ላይ አሁን እየተገበያዩ ያለበትን ዋጋ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
3. ከገቢ መጠን አንፃር (Income Method)
ይህ መንገድ የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ የሚተምነው የአእምሯዊ ንብረቱን በቢዝነስ ውስጥ በምንጠቀምበት ወቅት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ከሚገመተው የገቢ መጠን አንፃር ነው፡፡ ገቢ ስንል የተለያዩ ነገሮችን ሊወክል የሚችል ሲሆን፤ የሽያጭ መጠንን፣ የተለያዩ ትርፎችን፣ የጥሬ ገንዘብ ፍሰትን (Cash flow)፣ የተቀነሰ (ቀሪ የሆነን) ወጪ ሊያካትት ይችላል፡፡
በዚህ የዋጋ ትመና ዘዴ ውስጥ የተለያዩ ንኡስ የትመና ዘዴዎች የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በታች አንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡
አጠቃላይ የንብረት መጠንን በማቀናነስ መተመን (Asset Deduction Method)
ይህ መንገድ የአንድን በቴክኖሎጂ የታገዘ ቢዝነስ አጠቃላይ ዋጋ በማስላት የሚደረግ ሲሆን፤ ከዛም ውስጥ ቴክኖሎጂው (አዕምሯዊ ንብረቱ) ያለውን ድርሻ ለይቶ በማውጣት የሚሠራ የዋጋ ግመታ ዓይነት ነው፡፡ በተለይም በመጀመሪያ የአንድን ቢዝነስ ዋጋ ለማስላት የተለያዩ የቢዝነሱን ንብረቶች በመጠቀም የሚመነጨውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (Cash flow) በማስላት፤ ከዚያ ቢዝነሱ ያለውን ገንዘብ ነክ ንብረቶች (Monetary Assets) እና ቁሳዊ ንብረቶች (Tangible Properties) (መሬት፣ ሕንፃ፣ ማምረቻ ቁሳቁሶች) የመሳሰሉ ከቴክኖሎጂው (አዕምሯዊ ንብረቱ) ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ንብረቶች በመቀነስ በመጨረሻም ቀሪው ሊዳሰሱ የማይችሉ ንብረቶችን (Intangible Properties) ዋጋ ነው ብሎ በማስላት የሚደረግ የዋጋ ትመና ዘዴ ነው፡፡
የሮያሊቲ ክፍያ እፎይታ ዘዴ፤ (Relief Royalty Method)
አንድ ድርጅት የሦስተኛ ወገን የሆነ የአእምሯዊ ንብረት መብት (ቴክኖሎጂ) ለመጠቀም ከባለቤቱ ፈቃድ ማግኘት ያለበት ሲሆን፤ለመጠቀም በሮያሊቲ መልክ የሚከፈል ክፍያ መክፈል ይኖርበታል፡፡ የዚህ ዘዴ እሳቤም መሰረት የሚያደርገው የአእምሯዊ ንብረት መብቱን (ቴክኖሎጂ) የመጠቀም ፈቃድ (Inlicensing) ለማግኘት የሚያወጣውን ወጪ የአንድን የአእምሯዊ ንብረት መብት ዋጋ ይወክላል የሚል ነው።
ቅናሽ የተደረገበት የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (Discounted Cash Flow (DCF)
ይህ የትመና መንገድ ከአእምሯዊ ንብረቱ ወደ ፊት በተወሰኑ ዓመታት ሊገኝ የሚችለውን ገቢ በመተንበይ እና ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን የገቢ መጠን (ጥሬ ገንዘብ) (Cash Flow) አሁን ላይ ያለውን ዋጋ (Present Value) በተገቢው የቅናሽ መጠን (Discounted rate) እንዲሰላ በማድረግ የሚሰራ የትመና መንገድ ነው፡፡
የአእምሯዊ ንብረት መብቶችን ዋጋ ለመተመን የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች በዋናነት ከላይ የተዘረዘሩት ሲሆኑ በዚህ ጽሁፍ ያልተካተቱ እንደ ከታሰበዉ በላይ የተገኘ ገቢ (Excess Earnings) ዘዴ፣ የተገኘ ተጨማሪ ትርፍ (Premium Profit) ዘዴ እና ሌሎች የተለያዩ የአእምሯዊ ንብረት ትመና ዘዴዎችም ይኖራሉ፡፡
በኢትዮጵያ የፈጠራ ባለሙያዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ቀዳሚው የፈጠራ ስራዎቻቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚውል የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የዜጎችን በፋይናንስ ስርዓቱ እኩል ተጠቃሚነት ለማጎልበት ታስቦ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በመያዣነት በመጠቀም የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ ቁጥር 1147/2012 በብሄራዊ ባንክ የፀደቀ ሲሆን በዚህ አዋጅ ተንቀሳቃሽ ንብረት ተብለው ከተመደቡት መካከል የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ይገኙበታል፡፡
ምንጭ፡ የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት እና የጃፓን ፓተንት ጽ/ቤት የመማሪያ ሞጁሎች