በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ስር ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች የቅጅና ተዛማጅ መብቶች፣ ፓተንቶች (የግልጋሎት ሞዴሎችን ጨምሮ)፣ ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች እና የንግድ ምልክቶች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ባለሥልጣን መ/ቤቱ እነዚህን ሦስት የአእምሯዊ ንብረት ዘርፎች የሚመሩበት አዋጆችን ያስተዳድራል፡፡ እነዚህም አዋጆች በአጭሩ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96፣ የፈጠራ፣ አነስተኛ ፈጠራና ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች አዋጅ ቁጥር 123/87 እና የንግድ ምልክት ምዝገባ እና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 ናቸው፡፡
- የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጥበቃ አርእስት ሥራ ይባላል፡፡ ሥራው ጥበቃ የሚደረግለት የቅጅ መብት የሚያድርበት ሆኖ በተገኘ ጊዜ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቅጅ መብት ጥበቃ የሚያገኘው በዚሁ አዋጅ መሠረት ስለሆነ ማንኛውም የቅጅ መብት ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በዚሁ አዋጅ መሠረት ነው፡ ፡ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሁለት አይነት መብቶች ጥበቃ ያገኛሉ፡፡ እነሱም የኢኮኖሚ መብቶችና የሞራል መብቶች ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ መብቶች የሚያስጠብቁት የሥራውን ገንዘባዊ ጥቅሞች ሲሆን የሞራል መብቶች ደግሞ የሞራል ጥቅሞችን ያስጠብቃሉ፡፡ የሞራል ጥቅሞች ከክብር እና ከግለ ሰብ ጋር የተቆራኙ ቁሳዊነት የሌላቸው ለሦስተኛ ወገን የማይተላለፉ መብቶች ናቸው፡፡
የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ሥራዎቹ ወጥ ከሆኑ እና ግዙፍነት ካገኙ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሕጉ ጥበቃ ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን ፓተንቶች እና የንግድ ምልክቶች የሕግ ጥበቃ ለማግኘት ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች የተለየ ሥነ ሥርዓት ይከተላሉ፡፡
- የፈጠራ፣ አነስተኛ ፈጠራና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁ 123/87
የኢትዮጵያ ፓተንት በፈጠራ፣ አነስተኛ ፈጠራና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁ.123/87 ይመራል፡፡ ስያሜውም እንዲሚገልጸው አዋጅ ቁ.123/87 የፈጠራ ፓተንት እና ሁለት የጥበቃ ጊዜያቸው አጭር የሆኑ የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ መብቶችን ይዟል፡፡ በዚህ አዋጅ ጥበቃ የሚያገኙ የፈጠራ ሥራዎች እንደአግባቡ አዲስነት ፈጠራዊ ብቃት እና ኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
በዚህም መሠረት የፈጠራ ፓተንት አዲስ፣ ፈጠራዊ ብቃት እና ቴክኒካዊ ተግባር ላላቸው የፈጠራ ሥራዎች ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች ደግሞ በኢንዱስትሪ ወይም በእደ ጥበብ ለሚሠሩ ለበርካታ አይነት ምርቶች ገጽታ ማሳመሪያ ንድፎች ወይም ልዩ መልክ ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች አዲስ መለስተኛ ቴክኒካዊ መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራ ሥራዎች በፈጠራ ብቃት ማነስ ምክንያት ፓተንት የማይሰጣቸው ወይም ለቴክኒካዊ መፍትሄ ብቻ ስለተዘጋጁ በኢንዱስትሪያዊ ንድፎች ጥበቃ የማይደረግላቸው በአነስተኛ ፈጠራ ወይም በግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ጥበቃ ያገኛሉ፡፡ ሦስቱም ፓተንቶች የተለያየ የመቀበያ መመዘኛ አሏቸው፡፡ አጭር የጥበቃ ጊዜ ያላቸው መብቶች ቀላልና ያልተወሳሰበ የምዝገባ ሥርዓት ሲኖራቸው የፈጠራ ፓተንት የመቀበያ መመዘኛ ግን ከዓለም አቀፍ የፓተንቶች ደረጃ ጋር ተመሳሳይ እና ጥብቅ ነው፡፡ የጥበቃ ጊዜው ለግልጋሎት ሞዴሎች እና ለኢንዱስትሪያዊ ንድፎች ከፈጠራ ፓተንት የጥበቃ ጊዜ ያጠረ ቢሆንም ሁሉም በሥራዎቹ ላይ የብቸኛ መብት በማስገኘት ረገድ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ስለዚህ የመብቶቹ ተገቢነት ተሞግቶ በአግባቡ ውድቅ ካልተደረገ ወይም ዓመታዊ ክፍያቸው ሳይከፈል ቀርቶ መብቶቹ ቀሪ ካልሆኑ ወይም ጥበቃው ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ተጠናቆ ሥራዎቹ የሕዝብ ንብረት ካልሆኑ በቀር ባለመብቶቹ የፀና መብት ይኖራቸዋል፡፡
- የንግድ ምልክት ምዝገባ እና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98
የንግድ ምልክት ምዝገባ እና ጥበቃ አሠራር በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 ይመራል፡፡ ምንም እንኳ የንግድ ምልክት ጥበቃን አስመልክቶ ሕገ መንግስቱ እንደ ፈጠራና የድርሰት መብቶች ግልፅ ድንጋጌ ባያስቀም ጥለትም የባለሥልጣን መ/ቤቱ ማመልከቻ በመቀበል አግባብባ ባለው ሕግ መሠረት አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ ሕግ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት የባለሥልጣን መ/ቤቱ ለምዝገባ የሚቀርቡለትን የንግድ ምልክት ማመልከቻዎች የፎርማሊቲ መመዘኛዎች ማሟላታቸውን፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል ከተቀመጡ መርሆዎች ጋር ተገናዝበው የቀረቡ እና ከሦስተኛ ወገን መብቶች አንፃር መቃወሚያ ምክንያቶች የሌሉ መሆኑ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ምርመራ ከቅድመ እና ድህረ ምዝገባ ተቃውሞ ሥነ ስርዓቶች ጋር ተዳምሮ የምዝገባ ሥርዓቱን ጠንካራ ያስብለዋል፡፡