የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ለአእምሯዊ ንብረት እሴቶች ዋስትና ይሰጣሉ

በፍቅረ ተስፋዬ

የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የሕግ ከለላ አግኝተው ወደ አእምሯዊ ንብረት መብት እስካልተለወጡ ድረስ ንብረታዊ እሴቶቹን የራስ አድርጎ የመጠቀም ፋይዳው እጅግ ያነሰ ነው፡፡ የባለቤቶቻቸው አሻራ ያረፈባቸው የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የመጠበብ (የጥበብ) እና የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ጥበብና ፈጠራ ደግሞ የምናብ ውጤቶች ናቸው፡፡ እውቀት ውስን ነው ምናብ ግን ዓለምን የሚሸፍን የለውጥ መዳረሻ በመሆኑ ምናብ ከዕውቀት ይሻላል (አልበርት ኢንስታይን)፡፡ አንድን ነገር በሃሳብ ውስጥ ማየት በምናብ ማየት ነው፡፡ ከእውነታ ላይ ከተገኙ ስሜቶች በመነሳት እውን ያልሆነ አዲስ ወይም ያልታየ ነገር ማሰብ ማየት ወይም ያልተለመደን ስሜታዊ ወይም ሃሳባዊ ምስል በአእምሮ ወይም በኀሊና ውስጥ መሳል ምናብ ነው፡፡ይህ የሰው ልጅ የአእምሮ ስራ ውጤት በሕግ እውቅና ተሰጥቶት ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ያም የአእምሯዊ ንብረት መብት በመባል ይታወቃል፡፡ 

አእምሯዊ ንብረት የሰው ልጅ የአእምሮ ውጤት በሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ያለ ሕጋዊ መብት እንደሆነ አዋጅ ቁጥር 320/1995 በትርጓሜው አመልከቶናል፡፡ ሕጋዊ መብቶቹም ፓተንትን፣ የንግድ ምልክትን የምስክር ወረቀትን፣ የቅጂ መብቶችን እንደሚጨምር አያይዞ ገልጾልናል፡፡ የሁለት ቃላት ጥምረት የሆነው «አእምሯዊ ንብረት» በብራንድ፣ በኢንዱስትሪያዊ ንድፍ፣ በፓተንት(ፈጠራ) አነስተኛ ፈጠራ ማለትም የግልጋሎት ሞዴልን ይጨምራል፤በሥነ ጥበብ ስራዎች ላይ ለፈሰሰ መዋዕለ ነዋይ ጥበቃ የሚያደርግ ሕጋዊ መድበል ነው፡፡ይህ ሕጋዊ መድበል ጥበቃ የሚያደርገው ግዙፍነት ሳይኖራቸው ዋጋ ላላቸው የተለያዩ አእምሯዊ ንብረት እሴቶች ነው፡፡

አእምሯዊ ንብረት ሃሳቦች፣ ፈጠራዎች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች፣ ቅቦች፣ ሃውልቶች፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ በቃላት፣ በእይታ፣ በሙዚቃ፣ በቲያትር የተገለጹ ስራዎች ወይም በአጭሩ ማንኛውም  የአእምሮ ስራ ውጤት (በአጠቃላይ ተግባራዊ መረጃ) ውጤቱ የንብረት መብት ያቋቋመ ይሁን አይሁን ግብሩ ከሚገለጽበት ልዩ ቁሳዊ ነገር ውጪ ህልውና ያለውን ነገር የሚገልፅ የሕግ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ አእምሯዊ ንብረት እሴቶች ግዙፍነት ሳይኖራቸው ዋጋ ያላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ሆኖም መጠበብ ወይም ፈጠራ ያለሕግ ጥበቃ ፍፁም የሆነ ባለቤትነት አያስገኝም፡፡   

የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የሕግ ከለላ ካለገኙ በስተቀር ለፈጠሯቸው ወይም ላመነጯቸው ሰዎች መጠቀሚያ የመሆናቸው እድል ያነሰ ነው፡፡ ምክንያቱም ንብረታዊ እሴቶቹን ለመፍጠር ከሚጠይቀው ወጪ ይልቅ እነሱን ለመቅዳት የሚያስፈልገው ዋጋ እጅግ ያነሰ በመሆኑ፣በቀላሉ በሌሎች ሊወሰዱ የሚችሉ በመሆኑና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ነው፡፡ስለዚህ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በአእምሯዊ ንብረት እሴቶች ላይ ያሉ ህጋዊ መብቶች በመሆናቸው ከአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የተለዩ ናቸው፡፡

የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ከአእምሯዊ እሴቶች የመጠቀም ሂደትን ለማመቻቸት እና ለማሳካት የተዘረጉ ሕጋዊ ሁኔታዎች ሲሆኑ የንግድ ምልክት፣የንድፍ፣የግልጋሎት ሞዴል፣የፓተንት ወይም የቅጂ እና ተዛማች መብቶች እውቀትን ወደ ንብረት መብት በመለወጥ እና ባለቤቱ ሌሎች ሰዎችን ከመብቶቹ የገበያና የንግድ አገልግሎት በመከልከል የሱ ብቻ የሚያደርግበት መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ብራንድ ወይም የንግድ ምልክት በገበያ ውስጥ በተመሳሳይ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች መካከል መሳከር እንዳይፈጠር በመከላከል፣ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን መልካም ስም እና ዝና በመጠበቅ እና የሸማቾችን የገበያ ምርጫ በመምራትና ጥቅማቸውን በመጠበቅ ለኢኮኖሚያዊ ውጤታማነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ወይም ንድፍ በበኩሉ ከዕቃዎች ቴክኒካዊ ዓላማ እና ግብር ውጪ ለዕቃዎች ውጫዊ ገጽታ ወይም ለልዩ መልካቸው ጥበቃ የሚያደርግ የገበያ ስትራቴጂ እና የብራንድ ገጽታ ያለው ነው፡፡ ፓተንት (የግልጋሎት ሞዴልን ይጨምራል) አስቀድሞ የማይታወቅን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ወይም በነበረው ፈጠራ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል አሠራርን ቀላል በማድረግና አኗኗርን በማዘመን፣ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማሳደግ ለማህበራዊ ኢኮኖሚ ብልፅግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ የሥነ ጥበብ ወይም የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የሚያስገኙ ስራዎችሙዚቃ፣ ድራማ፣ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብና ሳይንሳዊ የአእምሮ ውጤቶች መንፈሳዊና ኢኮኖሚያው ፋይዳቸው ጥልቅና የሰፋ ነው፡፡ አሁን አብይ የሆነው ጥያቄ መብቶቹ እንዴት ይቋቋማሉ የሚለው ነው፡፡

የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ግዙፋዊ ህልውና የሌላቸው፣በአምስቱ የስሜት ህዋሳት መኖራቸው የማይታወቅ፣በመጠን፣በዓይነት በአካል የማይያዙ ወይም በያዙት ቦታና አንፃራዊ አዋሳኞች የሚገለጹ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያላቸው ቁልፍ ቦታ እንዳይታይ ሁነኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፤አሁንም ነው፡፡ በመሆኑም የንብረት መብት ጥያቄ በሕግ እውቅና እንዲያገኝ እያንዳንዱ የአእምሮ ስራ ውጤት ተጨባጭነት ባለው መልክ ተለይቶ እንዲወሰን መመዘኛ ማስቀመጥ የሕጉ ሃላፊነት ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ስራዎቹ ሊታዩ፣ ሊደመጡ፣ መኖራቸው ሊታወቅ በሚቻልበት አኳኋን፣ የመወከያ ዘዴ፣ የምዝገባ ሥርዐቶች እንደ ፓተንት መግለጫ፣ የመብት ወሰኖች፣ ሥዕሎች ስለፈጠራው በቂ ማብራሪያና መመሪያ ማስቀመጥ የመሳሰሉትን ሊጨምር ይችላል፡፡ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በምዝገባ ሥርዓት አማካይነት ወይም ስራዎቹ በመውጣታቸው ብቻ የሕግ ጥበቃ ሊያገኙ የሚችሉ ናቸው፡፡   

በስራው መውጣት ብቻ ስለሚገኙ መብቶች    

በሥነ ጥበብ እና ሳይንሳዊ መስኮች የሚወጡ ሥራዎች ሥራው በመውጣቱ ብቻ ጥበቃ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ይህም እውን የሚሆነው ሁለት መመዘኛዎች ተሟልተው ሲገኙ እንደሆነ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ያመለክተናል፡፡ እነሱም የሥራው ወጥ/ኦሪጂናል/ መሆን እና መቀረፅ ወይም ግዙፍነት ማግኘት ናቸው፡፡ የአዋጁም ሃይለ ቃል የሥራው ዓላማና የጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ሥራው ወጥ/ኦሪጂናል/ ከሆነ እና ከተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራውን በማውጣት ብቻ የሥራ አመንጪው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ ያገኛል ይላል፡፡[1] መቀረፅ ወይም ግዝፍት ማግኘትሥራው በጽሑፍ ወይም በቁሳዊ ዘዴ ወይም መቅረፀ ብልሀት ግዝፈት ማግኘቱን የሚያስብ መመዘኛ ነው ፡፡[2] የዚህ መመዘኛ ጠቀሜታ በዋናነት ለሕጋዊ ማስረጃነቱ ነው፡፡ በጽሑፍ ያልኖረ ሥራ በማስረጃነት ተቀባይነት የለውም የማይባል ቢሆንም እንኳ በትውስታ የማይታወቅ ወይም ተደጋግሞ እንዲታይ በሚያደርግ ዘዴ ወይም መሳሪያ ያልቀረበን ሥራ የመብት ጥሰት ተደርጎበታል ብሎ ለማስረዳትም ሆነ ለመወሰን አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ሥራው ለንፅፅር መቅረብ በሚችልበት አኳኋን መገኘቱ በተለይ ለፍርድ ቤቶች የማስረጃ ጠቀሜታ አለው፡፡[3] ሕጉ ምንጊዜም ግዝፈት ከሌለው ነገር ይልቅ ግዝፈት ላለው ማስረጃ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አንድ ሥራ የቅጂ መብት የሚያድርበት መሆኑን ለመወሰን አይነተኛ መስፈርት ሆኖ የሚያገለግለው የወጥነት/ኦሪጂናሊቲ/ መመዘኛ ነው፡፡

ከላይ እንደተመለከተው የሥራው ዓላማና የጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ሥራው ወጥ/ኦሪጂናል/ ከሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ ያገኛል፡፡ ነገር ግን የወጥነት መመዘኛ በአዋጁ ትርጉም የተሰጠው ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አንድ መቁረጫ ዘዴ ማስቀመጥ ያስቸግር ይሆናል፡፡ ቢሆንም የሕጉን መንፈስ በተሻለ ለማገናዘብ የቃሉ የመዝገበ ቃላት ትርጉም ያሻ ይሆናል፡፡ «ወጥ» ከሃሳብ፣ ከድርሰት ጋር በተገናኘ አዲስ፣ ያልተቀዳ፣ ያልተኮረጀ ማለት ነው (የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፡ 1993 ዓ.ም)፡፡ በሌላ በኩል የቃሉ አቻ ሆኖ የተመለከተው «ኦሪጂናል» የእንግሊዘኛ ቃል አዲስ፣ ቀድሞ ከነበረው የተለየ፣ ያልተቀዳ ወይም ፎቶኮፒ ያልሆነ ማለት ነው( የOxford Advanced Learners Dictionay (8th ed.)፡፡ ሁለቱም ትርጉሞች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው አዋጁም አማራጭ አድርጎ ስላስቀመጠው ወጥ /ኦርጂናል/ ማለት አዲስ፣ ቀድሞ ከነበረው የተለየ፣ ያልተቀዳ፣ ያልተኮረጀ ሥራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ የአዋጁ የወጥነት መመዘኛ አዲስ ወይም የተለየ ሥራ ለመስራት አስፈላጊ መረጃዎችን ከሌሎች ሥራዎች ወይም ከሕዝብ ንብረት እውቀቶች ወይም ሥራዎች ምክንያታዊ በሆነ መጠን መውሰድን የሚከለክል አይደለም፡፡መመዘኛው ሥራው የሥራ አመንጪው የግል የፈጠራ ሥራ መሆኑን ማረጋገጥ የሚሻ እንጂ ሥራው እፁብ ድንቅ መሆኑን፣ የመጠበብ ብቃትና ጥራት ወይም መልካምነት ያለው ወይም  ሃሳብ የወለደው መሆኑን የመፈተሽ ፍላጎት የለውም፡፡[4] ቢሆንም ርባና የሌለው የሃሳብ አገላለጽ ወይም አእምሮሯዊ ክሂሎትና ጥረት ያልተካተተበት ዋጋ ቢስና ከንቱ ልፋት እንደ ሥራ ተቆጥሮ ጥበቃ ያገኛል ማለት አይደለም፡፡[5] ምክያቱም ዓላማ የሌለው ሥራ ፋይዳ የማይኖረው በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ የወጥነት መመዘኛን ከፓተንት የአዲስነት መመዘኛ አንፃር ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ፓተንት ለማግኘት መሟላት ካለባቸው መመዘኛዎች መካከል አንዱ የፈጠራው አዲስ መሆን ነው፡፡ ይህ መመዘኛ የፈጠራ ሥራውን ከቀደምት ጥበብ ጋር በማስተያየት አዲስ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን የሚጠቅም ሲሆን የወጥነት ፍለጋ ግን ሥራው የሥራ አመንጪው የግል የሥራ ውጤት (ያልተቀዳ) መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ከሌላ ሰው ያልተቀዱ የሥራ አመንጪዎቹን የግል ጥረት የሚያሳዩ ሥራዎች በአጋጣሚ ተመሳሳይ ቢሆኑ የሥራ አመንጪዎቹ ለየራሳቸው ሥራ የቅጂ መብት ባለቤት መሆናቸው አይከለከልም፡፡ ነገር ግን ይህ በፓተንት ህግ የተፈቀደ አይደለም፡፡ ሁለት ሰዎች ለየራሳቸው አንድ ዐይነት ፈጠራ ሠርተው ፓተንት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁ ፓተንት የማግኘት መብት ያለው ማመልከቻውን መጀመሪያ ላስገባው ሰው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የሕጉ መርህ መጀመሪያ የመጣ ይስተናገዳል መጀመሪያ ስለሚል የመጀመሪያው ማመልከቻ የሁለተኛውን ማመልከቻ አዲስነት ያሳጣዋል፡፡ ፈጠራው አዲስነት ከሌለው ደግሞ በምዝገባ ሥርዓቱ ፓተንት የሚሰጠው አይሆንም፡፡ 

በምዝገባ ሥርዓት ስለሚገኙ መብቶች

በምዝገባ ሥርዓት መብት የሚገኝባቸው የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በኢንዱስትሪያዊ ንብረት ፈርጅ ስር ያሉትን ይይዛል፡፡ እንዱስትሪያዊ ንብረት ከመነሻው ቴክኖሎጂዎችን፣ እንዱስትሪዎችን እና የንግድ ሥራዎችን ወደፊት ለማራመድ ተብሎ የተፈጠሩ እንደ ፓተንቶች (ፈጠራዎች) ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች፣ የንግድ ምልክቶች፣የአገልግሎት ምልክቶች፣የትእምርተ አካባቢዎችን /Geographical Indications/ይጨምራል፡፡ የምዝገባ ሥርዐት ለአንዳንዶቹ ቀላል ለአንዳንዶቹ ደግሞ ውስብስብና ጥብቅ የቅበላና የምርመራ ሥነ ሥርዓቶች ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡

የማመልከቻ ቅበላና የምርመራ ሥነ ሥዓቶች በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ እንዲሁም በፓተን አዋጅ ተካተው ይገኛሉ፡፡ የንግድ ምልክት ማመልከቻ ቅበላና ምርመራ ሥነሥርዓቶች እንደፓተንት የጠበቁና የተወሳሰቡ ባይሆኑም ሙሉ ምርመራ የሚደረግባቸው ሆነው እናገኛቸዋልን፡፡ በዚህም መሠረት ከማመልከቻ ቅበላ (ፎርማሊቲ) እስከ መብቶቹ ተገቢነት (ሥረ ነገር) ፍተሻ የሚደረግባቸው ናቸው፡፡

ፎርማሊቲን በተመለከተ አስፈላጊ ሰነዶች በተሟላ መጠንና ዐይነት መኖራቸው ክፍያዎች እንደደንቡ የተፈጸሙ መሆናቸው የሚጣራ ይሆናል፡፡ የሥረ ነገር ምርመራ የንግድ ምልክቱ ለተፈለገበት ተግባር ብቁ መሆኑን፣ የጠቅላላውን እና የንግዱን ማህበረሰብ ጥቅም በመፃረር ጉዳት የማያደርስ እና የሦስተኛ ወገን መብቶችን የማይጋፋ መሆኑ በምርመራው የሚጣራ ይሆናል፡፡ የእነዚህን ሥነ ሥርዓቶች ውጤታማነት ለማጠናከር ደግሞ አዋጁ ሁለት ወሳኝ ሥነ ሥርዓቶችን አስቀምጧል፡፡ እነሱም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ማንኛውም ሰው ለምዝገባ የቀረቡ ማመልከቻዎችን ተቃውሞ የሚያሰማባቸው እና የምርመራ መመዘኛዎቹ ትኩረት ሳይሰጣቸው ቀርቶ የተመዘገቡ ማመልከቻዎች ጥቅም አለን በሚሉ ማናቸውም ሰዎች መብቶቹ እንዲሻሩ ጥያቄ የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡ ሌላው የፓተንት ቅበላና ምርመራ ሥነ ሥርዓቶችን ይመለከታል፡፡

   

የአዋጅ ቁጥር 123/1987 አጭር ርዕስ እንደሚጠቁመው የኢትዮጵያ የፓተንት ሥርዓት የአስገቢ ፓተንትን ጨምሮ የፈጠራ ፓተንት፣ አነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርቲፊኬት መብቶችን ይዞ አጠቃላይና ልዩ የቅበላና ምርመራ ሥነ ሥርዓቶች አሉት፡፡ የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪያዊ ንደፍ ሰርቲፊኬቶች ቀላል እና ያልተወሳሰቡ ሥነ ሥርዓቶች ሲኖሯቸው የፈጠራ ፓተንት ቅበላና ምርመራ ከዓለም አቀፍ ሥነ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መልኩ ጥብቅና ውስብስብ ናቸው፡፡

አንድ ፈጠራ ለፓተንት ጥበቃ ብቁ እንዲሆን የፈጠራው ርዕሰ-ጉዳይ ፓተንት የሚሰጥበት፣ የፈጠራ ሃሳቡ አዲስ፣ ተግባራዊ ጠቀሜታ እና ፈጠራዊ ብቃት ያለው፣ ፈጠራው በአግባቡ ገሀድ የተደረገ (የፈጠራው ምንነትና አሠራር የተብራራ) መሆኑ እና ፈጠራው ከምርት ወይም ከአሠራር ሂደት ጋር በተያያዘ በሁሉም የቴክኖሎጂ መስኮች(ልዩ ሁኔታዎች ተጠብቀው) ፓተንት የሚሰጥ መሆኑ በፓተንት ሥርዓታችን የተጠበቀ መርህ ነው፡፡ ነገር ግን መመዘኛዎቹ ተመሳሳይ ቢሆኑም የተለያዩ ደረጃዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ፈጠራዊ ብቃት በሁሉም አገራት ያለ መመዘኛ ነው ነገር ግን የፈጠራው ብቃት ደረጃ ሊለያይ ይችላል፡፡ ሲጠቃለል ማንኛውም የፈጠራ ፓተንት መመዘኛ የፓተንት ሥርዐቱ የተመሠረተበትን መርሆና ፖሊሲ እውን ለማድረግ የሚያገለግል በመሆኑ በቂና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፡፡ ነገር ግን በቴክኖሎጂ መስክ የሚደረግ የፈጠራ እንቅስቃሴ እምብዛም በማይታወቅባቸው እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት ጥብቅና ውስብስብ የፓተንት ቅበላና ምርመራ ሥርዓቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አያሌ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አነስተኛ ፈጠራዎችን ማበረታታት የፓተንት ሥርዓቱ ዐይነተኛ ባህሪይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ የፓተንት ሥርዓትም በዚሁ መንፈስ የተቀረፀ ስለሆነ የአነስተኛ ፈጠራ ሰርቲፊኬት አማራጭ አለው፡፡ ይህ አማራጭ በአንድ በኩል ለፓተንት ጥበቃ ብቃት የሌላቸው የፈጠራ ሥራዎች ውድቅ ከሚሆኑ ይልቅ ለማበረታታት በሌላ በኩል ለፓተንት ጥበቃ ብቃት የሌላቸው የፈጠራ ሥራዎች ፓተንት እየተሰጣቸው የፓተንት ሥርዓቱን ደረጃ ዝቅ እንዳይል ለመከላከል ነው፡፡ እነዚህን ታሳቢ አድርጎ የሚደረገው ምርመራ አነስተኛ ፈጠራው ተግባራዊ (ቴክኒካዊ) ግብር ያለው መሆኑ፣ ለጠቅላላው መልካም ጠባይና ሰላም ተፃራሪ አለመሆኑ፣ የመብት ወሰኑ በግልፅ እና በትክክል የተሞላ መሆኑ፣ መግለጫውና የሥዕል አደራረጉ በአግባቡ መሆኑና ግልፅነት የጎደለው አለመሆኑ ሲረጋገጥ ሰርቲፊኬት ይሰጣል፡፡  የግብይት ወረታቸው ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭ የሆኑ የኢንዱስትሪያዊ ንድፎችም ቀላል እና ፈጣን የምዝገባ ሥርዓት አላቸው፡፡

ለምዝገባ የቀረበው የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ በትክክል ንድፍ መሆኑ ሲረጋገጥና ከላይ ለአነስተኛ ፈጠራ የተዘረዘሩ መመዘኛዎች በተመሳሳይ ለንድፍ ተግባራዊ ሆነው ንድፉ ተቀባይት ሲያገኝ ሰርቲፊኬት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ምንም እንኳ የጥበቃ ሥርዓቶቹ በኢትዮጵያ የተመቻቹ ባይሆንም በአብዛኛው ለገጠሩ ህብረተሰብ ኑሮ መሻሻል ዓይነተኛ ድርሻ ያላቸው የትእምርተ አካባቢዎች እና የነባር እውቀት ሥርዓቶችን ለማቆም የሕግ ማርቀቅ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

የመልከዐ ምድር አመላካቾች ምርቶች በዐይነታቸው ወይም በጣዕማቸው ወይም በሌላ መለያ ባህሪያቸው ምክንያት የተለየ የገበያ ተፈላጊነት አላቸው፡፡ የምርቶቹ መገኛ አካባቢዎች ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ነገሮች በምርቶቹ ውስጥ ባሳደሩት ልዩ ባህሪይ የአካባቢዎቹ መጠሪያ ወይም ሌላ ገጽታቸው ለምርቶቹ መጠሪያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ለምሳሌ የይርጋ ጨፌ ቡና፣ የባቦጋያ ቡና፣ የማረቆ በርበሬ፣ የሸኖ ቅቤ፣ የመንዝ በግ ወዘተ…ሲባል እንሰማለን፡፡ እንግዲህ በምርቶቹ ውስጥ ያደረው የአካባቢዎቹ ልዩ ባህሪይ በምርቱና በአካባቢው መካከል የትስስር ምክንያት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ልዩ ጣእም ወይም ባህሪይ ለምርቱ የገበያ ዕድል ፈጣሪና የአእምሯዊ ንብረት እሴት ክፍል የሆነው ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ነባር እውቀቶች ባለብዙ ዘርፍ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፋይዳ ያላቸው የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች ናቸው፡፡ 

ነባር እውቀት/Traditional knowledge/ ባህላዊ መሠረት ያለውና ከግብርና ስራ፣ ከአካባቢ እንክብካቤ፣ ከጤና አጠባበቅ፣ ከአገር በቀልና ከነባር የህክምና እውቀት፣ ከብዝሀ ህይወት እና ከነባር የአኗኗር ዘይቤ፣ ከተፈጥሮ እና እፀ ስሪት (ጀንቲክ) ሃብቶች፣ ከነባር የስነ ህንጻ እውቀትና ብልሃት እንዲሁም ከግንባታ ቴክኖሎጂ እውቀት ጋር ትስስር ያለው ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ እየተዘጋጀ ባለው እረቂቅ አዋጅ የማህበረሰብ እውቀት ተብሎ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ቃሉ ጊዜንና የእውቀት ባለቤትነትን በግልፅ ስለማያሳይ ነባር እውቀት ለዚህ አጭር ማስታወሻ ተመርጧል፡፡ የነባር እውቀት እሴቶች የሕግ ጥበቃ ዓላማ እሴቶቹ ከባህላዊ ማዕቀፋቸው ወይም ከልማድና ወጋቸው ውጪ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የማይገባ ጥቅም መሰብሰቢያ እንዳይሆኑ ለመከላከል ነው፡፡ 

ሲጠቃለል የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች ለፈጠሯቸው ወይም ላመነጯቸው ሰዎች መገልገያ ሊሆኑ የሚችሉት በንግድ ምልክቶች፣ ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች፣ ፓተንቶች፣ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች እና ረቂቅ አዋጆቹ ሲጸድቁ የትእምርተ አካባቢዎች የነባር እውቀት እሴቶች በሕግ አስተማማኝ ዋስትና ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡


[1] የአዋጁ አንቀጽ 6

[2] የአዋጁ አንቀጽ 6 (ለ)

[3] ኢሰይን የናይጀሪያ የቅጂ መብት ሕግ ገጽ 80

[4]  በንቲሊይ እና ሸርማን ገጽ 92

[5] በንቲሊይ እና ሸርማን ገጽ 92

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS