ንግድ ምልክትን የማስመዝገብ ትሩፋቶች

በወንድወሰን ሂርጶ

በአለም አቀፍ ንግድ ስምምነት አንቀጽ 41 መሰረት የንግድ ምልክት መብቶችን ማስከበር ሂደቶች ያልተወሳሰቡ፣ መዘግየት የማይታይባቸውና ለሁሉም ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎችም ቢሆኑ በቀረበላቸው ማስረጃ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ እንዲሁም በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅሬታ ያለው ወገን የይግባኝ መብቱ መጠበቅ እንዳለበት ይገልጻል፡፡  

የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ስነስርዓት ህጎችም ቢሆኑ ከላይ ከተገለጸው የአለም አቀፍ የንግድ ስምምነት የራቀ ህግ የላቸውም፡፡ይልቁንም በአመዛኙ ከላይ የተገለጹትን ነጥቦች አሟልተው የያዙ ናቸው፡፡በሀገራችን የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ የሚከናወነው አዋጅ ቁጥር 501/1998ን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 49 መሰረት አዋጁን መሰረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮች አና ተዛማጅ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን የፌደራል ፍ/ቤቶች እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ነገር ግን ስነስርዓታዊ ጉዳዮች ላይ የሚጠቀሙት ከአጼ ሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በስራ ላይ ያሉትን የፍትሐ ብሔር እና የወንለኛ ሰነስርዓት ህጎችን ነው፡፡

በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/1998 መሰረት ፍርድ ቤቶች ካላቸው ስልጣን ውስጥ ከአንቀጽ 39 እስከ 42 የተመለከቱት ናቸው፡፡ በእነዚህ አንቀጾች መሰረት የንግድ ምልክት መብት ጥሰት ሲኖር ይህንን በፈጸመው ግለሰብ ላይ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ውሰጥ አስተዳደራዊ፣የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚኖር ያመለክታል፡፡ 

በአንቀጽ 39 መሰረት የንግድ ምልክት መብት ባለቤት የሆኑ ሰዎች ማግኘት ከሚችሉት ነገሮች ወስጥ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉት እቃዎች ላይ ጊዜያዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነው፡፡ይህ መብት በአለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ውስጥ በግልጽ የተደነገገ ነው፡፡ የጊዜያዊ እርምጃዎች መሰረታዊ አላማ የመብት ገሰሳን ለመከላላል በተለይም ገቢና ወጪ እቃዎች የጉምሩክ ስነ ስርዓቶችን አልፈው ወደ ገበያ እንዳይገቡ ለማድረግና የመብት ገሰሳ ፈጽሟል የተባለውን ዕቃ እንደማስረጃ ለመያዝ እንደሆነ አንቀጽ 39 (1)(ሀ) (ለ) ይገልጻል፡፡ ይህ እርምጃ ሲወሰድ ተከሳሹ እርምጃው መወሰዱን ወዲያውኑ እንዲያውቀው መደረግ እንደሚኖርበት ይህ አንቀጽ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ ገቢና ወጪ እቃዎች በጊዜያዊነት የማቆየት እርምጃ የሚወስደው የኢትዮጵያ  የጉምሩክ ኮሚሽን ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው የንግድ ምልክቱ ባለቤት፤ የምዝገባ ምስክር ወረቀት እና ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎችን ከማመልከቻ ጋር ለጉምሩክ ኮሚሽን በማቅረብ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ የምስክር ወረቀት የቀረበለት የጉምሩክ ኮሚሽን የመብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉትን ዕቃዎች ይዞ ማቆየት የሚችለው እቃው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ለአስር ቀናት ብቻ ነው፡፡የንግድ ምልክቱ ባለቤት በእነዚህ አስር ቀናት ውስጥ የፍርድ  ቤት እግድ ይዞ ማምጣት ካልቻለ የተያዘው ዕቃ ይለቀቅና ለዋስትናም ያስያዘው ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ይሆናል፡፡የድንበር ላይ እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ቢሆን እቃዎች እንዲያዙ ሲጠየቁ ከብቸኛ አስመጪ ጋር  የማያያዝ ችግሮች የሚታዩ ናቸው፡፡

የንግድ ምልክት ምዝገባ ከሚያስገኘው ሌላው ጥቅም ውስጥ የመብት ጥሰት ፈጻሚው ላይ የፍትሐ ብሔር እርምጃዎችን ማስወሰድ ነው፡፡በአዋጅ ቁጥር 501/1998 አንቀጽ 40 መሰረት   ፍርድ ቤት የመብት ጥሰቱ እንዲቆም ቋሚ ትዕዝዛ መስጠት እና የመብት ጥሰቱ በመፈጸሙ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ከሳሽ (የንግድ ምልክቱ ባለቤት) እንዲካስ ማድረግ ነው፡፡በዚህ አንቀጽ መሰረት ፍርድ ቤቱ የጉዳት ካሳ ሲወስን ተከሳሹ የንግድ ምልክቱን በመጠቀም ያገኘው የተጣራ ትርፍና የንግድ ምልክቱን እንዲጠቀም ተፈቅዶለት ቢሆን ኖሮ ሊከፍለው ይችለው ከነበረው መካከል የበለጠውን እንዲከፍል ይወስናል፡፡ሕጉ ይሀንን ቢልም   የተከሳሾችን የሂሳብ ሪፖርት ለማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ ሲሆን ይታያል፡፡

የንግድ ምልክት መብት ጥሰት የሚያስከትለው ሌላው ኃላፊነት የወንጀል ተጠያቂነት ነው፡፡ የተመዘገበ የንግድ ምልከትን መብትን ሆነ ብሎ የተጠቀመ ሰው ከአምስት ዓመት በማያንስ ከአስር አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡የመብት ጥሰቱ በጎላ ቸልተኝነት የተፈጸመ ከሆነ ደግሞ ከአንድ ዓመት ባላነሰ ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡የንግድ ምልክት ወንጀሎችን የሚያጣራው የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሲሆን ከንግድ ምልክት ባህሪ መነሻነት አኳያ አንዳንድ የማጣራት ሂደቶች ሲዘገዩ የሚታይ ሲሆን ፍርድ ቤቶችም ባልዘገየ ሁኔታ ውሳኔ ሲሰጡ አይታይም፡፡እዚህ ላይ መገንዘብ   የሚገባው ነጥብ የአዕምሯዊ ንብረት ጉዳዮች በጠቅላላው በተለይም የንግድ ምልክት ወንጀሎች በኣፋጣኝ መጣራት እና ውሳኔ ማግኘት ያለባቸው ናቸው፡፡

የንግድ ምልክት መብትን የማስከበር ሂደት ስለ ንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2013 ይደገፋል፡፡ ይህ አዋጅ   የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ያቋቋመ ሲሆን የተመዘገበ የንግድ ምልክት ያለው ግለሰብ አቤቱታ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በማቅረብ የመብት ጥሰት የፈጸመው ግለሰብ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ይገልጻል፡፡ይህ አስተዳደራዊ ቅጣትም ከዓመታዊ ሽያጭ ላይ ከ5 -10 በመቶ እንደሆነ አዋጁ ያስገነዝባል፡፡

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS