በፍሬው ተገኝ
የአእምሯዊ ንብረቶች መብቶች (Intellectual Property Right) ከምንላቸው ዋና ዋናዎቹ የቅጂ መብትና ተዛማጅ መብቶች፣ፓተንት እና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሲሆኑ በእነዚህ ዘርፎች የብቸኝነት መብትን (Exclusive right) የሚያገኙ ስራዎች(ነገሮች) በጥቅሉ ሊዳሰሱ የማይችሉ ንብረቶች (Intangible Properties) ተብለው የሚታወቁ ሲሆን ልክ እንደ ማንኛውም ቁሳዊ ንብረት (Tangible Properties) ንብረቶቹን የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማከራየት እንዲሁም በሌላ በማናቸውም መንገድ ለሌሎች የማስተላለፍ መብትን የሚያስገኝ ሲሆን በተቃራኒው ሦስተኛ ወገኖች ያለባለመብቱ ፈቃድ ከላይ የተዘረዘሩትን ድርጊቶች ፈፅመው ሲገኙ በህግ መጠየቅ የሚያስችለው ነው፡፡
የአእምሯዊ ንብረቶች መብቶች ሊታዩ (ሊዳሰሱ) የማይችሉ ንብረቶች በመሆናቸው እና ኢኮኖሚያዊ ውጤታቸውን ለማስገኘት ደግሞ የተለያዩ ቁሳዊ ሃብቶችን እና ሌሎች ግብአቶች የሚጠቀሙ በመሆናቸው በመጨረሻ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ውስጥ ምን ያክሉ በአእምሯዊ ንብረት መብቶች ምክኒያት እንዲሁም ምን ያክሉ በተጠቀሟቸው ቁሳዊ ሃብቶችና ግብዓቶች የመነጨ እንደሆነ ለመየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም አብዛኛውን የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ይህን ያህል ዋጋ ያወጣሉ ብሎ በቀላሉ ለመተመን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ባለሙያዎች የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ዋጋ ከሌሎች ቁሳዊ ንብረቶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የትመና ንድፈ ሃሳቦችንና ዘዴዎችን ለአእምሯዊ ንብረት መብቶች በሚስማማ መልኩ በማስተካከል የአእምሯዊ ንብረት የዋጋ ትመናን ማድረግ ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የአእምሯዊ ንብረት የዋጋ ትመናን በሶስት ዓበይት መንገዶች ማድረግ የሚቻል ሲሆን፡- እነሱም፡-
- ከወጪ አንፃር (Cost Method)
- ከገበያ ዋጋ አንፃር (Market Methods)
- ከገቢ መጠን አንፃር (Income method)
ሲሆኑ በውስጣቸው ደግሞ ሌሎች ንኡስ የትመና ዘዴዎችን የሚያካትቱ ሲሆን ከዚህ በታች አጠር ባለመልኩ ለማየት እንሞክራለን፡፡
- ከወጪ አንጻር (Cost Method)
ይህ መንገድ የአእምሯዊ ንብረትን (ምሳሌ፤ ቴክኖሎጂን) ዋጋ የመተመኛ መንገድ፣ የአእምሯዊ ንብረቱ ባለቤት ለመሆን ወይም ንብረቱን ለማፍራት የወጣውን ወጪ መሠረት በማድረግ የሚደረግ የትመና ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ፈጠራን (የአእምሯዊ ንብረትን) ከወጪ አንፃር በመተመን መንገድ ውስጥ ሁለት መንገዶች ያሉ ሲሆን፡-
‹‹የታሪካዊ ወጪ መንገድ›› (Historical cost approach) የሚባለው አንዱ ሲሆን፤ ይህም የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ ለመተመን የአእምሯዊ ንብረቱን(ቴክኖሎጂውን) ለመፍጠር፣ ለማምረት (ለማበልፀግ) ከመጀመሪያው ጀምሮ በምርምርና መሰል ተግባራት የወጣውን ወጪ በሙሉ በመደመር የአእምሯዊ ንብረቱ(ቴክኖሎጂው) ዋጋ ነው ብሎ ግምት በመውሰድ የመተመኛ መንገድ ነው፡፡
ሌላኛው መንገድ ለመተካት የወጣ ወጪ መንገድ፤ (Replacement Cost Approach) ሲሆን፤ የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ የሚያሰላው ሊተመን የታሰበውን የአእምሯዊ ንብረት ወደፊት እንደ አዲስ እንፍጠረው፣እንግዛው (እናበልፅገው) ብለን በምናባችን በማሰብ ለዚህ የሚያስፈልገውን የወደፊት ወጪ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከግምት በማስገባት የአእምሯዊ ንብረትን የመተመኛ መንገድ ነው፡፡
- ከገበያ ዋጋ አንፃር መተመን (Market Methods)
ይህ ከገበያ ዋጋ አንፃር የመተመን ዘዴ ተመሳሳይ የሆኑ የአእምሯዊ ንብረቶች ከዚህ በፊት በገበያ ላይ በምን ያህል ዋጋ እየተሸጡ እንዳሉ እና የእነዚህንም ግብይቶች ዋጋ አሁን ላይ ለመተመን የተፈለገውን የአእምሯዊ ንብረት ለመተመን እንደ መነሻ በመውሰድ የሚደረግ የትመና ዓይነት ነው፡፡ ተነፃፃሪ (ተመሳሳይ) የሆኑ የአእምሯዊ ንብረቶች (ቴክኖሎጂዎች) በገበያ ላይ በአሁን ሰዓት እየተገበያዩ ያለበትን ዋጋ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
- ከገቢ መጠን አንፃር (Income Method)
ይህ መንገድ የአንድን የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ የሚተምነው የአእምሯዊ ንብረቱን በቢዝነስ ውስጥ በምንጠቀምበት ወቅት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ከሚገመተው የገቢ መጠን አንፃር ነው፡፡ ገቢ ስንል የተለያዩ ነገሮችን ሊወክል የሚችል ሲሆን፤ የሽያጭ መጠንን፣ የተለያዩ ትርፎችን፣ የጥሬ ገንዘብ ፍሰትን (Cash flow) ፣ የተቀነሰ (ቀሪ የሆነን) ወጪ ሊያካትት ይችላል፡፡
በዚህ የዋጋ ትመና ዘዴ ውስጥ የተለያዩ ንኡስ የትመና ዘዴዎች ያሉ ሲሆን ፤
አጠቃላይ የንብረት መጠንን በማቀናነስ መተመን (Asset Deduction Method) ይህ መንገድ የአንድን በቴክኖሎጂ የታገዘ ቢዝነስ አጠቃላይ ዋጋ በማስላት የሚነሳ ሲሆን፤ ከዛም ውስጥ ቴክኖሎጂው (አዕምሯዊ ንብረቱ) ያለውን ድርሻ ለይቶ በማውጣት የሚሠራ የዋጋ ግመታ ዓይነት ነው፡፡ በተለይም በመጀመሪያ የአንድን ቢዝነስ ዋጋ ለማስላት የተለያዩ የቢዝነሱን ንብረቶች በመጠቀም የሚመነጨውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (Cash flow) በማስላት፤ ከዚያ ቢዝነሱ ያለውን ገንዘብ ነክ ንብረቶች (Monetary Assets) እና ቁሳዊ ንብረቶች (Tangible Properties) (መሬት፣ ሕንፃ፣ ማምረቻ ቁሳቁሶች) የመሳሰሉ ከቴክኖሎጂው (አዕምሯዊ ንብረቱ) ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ንብረቶች በመቀነስ በመጨረሻም ቀሪው ሊዳሰሱ የማይችሉ ንብረቶችን (Intangible Properties) ዋጋ ነው ብሎ በማስላት ነው፡፡
የሮያሊቲ ክፍያ እፎይታ ዘዴ፤ (Relief Royalty Method)
አንድ ድርጅት የሦስተኛ ወገን የሆነ የአእምሯዊ ንብረት መብት (ቴክኖሎጂ) ለመጠቀም ከባለቤቱ ፈቃድ ማግኘት ያለበት ሲሆን፤ለመጠቀም በሮያሊቲ መልክ የሚከፈል ክፍያ መክፈል ይኖርበታል፡፡ የዚህ ዘዴ እሳቤም መሰረት የሚያደርገው የአእምሯዊ ንብረት መብቱን (ቴክኖሎጂ) የመጠቀም ፈቃድ (In-licensing) ለማግኘት የምናወጣው ወጪ የአንድን የአእምሯዊ ንብረት መብት ዋጋ ይወክላል የሚል ነው፡፡
ቅናሽ የተደረገበት የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (Discounted Cash Flow (DCF))
ይህ የትመና መንገድ ከአእምሯዊ ንብረቱ ወደ ፊት በተወሰኑ ዓመታት ሊገኝ የሚችለውን ገቢ በመተንበይ እና ይገኛል ተብሎ የታሰበው የገቢ መጠን (ጥሬ ገንዘብ) (Cash Flow) አሁን ላይ ያለውን ዋጋ (Present Value) በተገቢው የቅናሽ መጠን (Discounted rate) እንዲሰላ በማድረግ የሚሰራ የትመና መንገድ ነው፡፡
በዋነኛነት የአእምሯዊ ንብረት መብቶችን ዋጋ ለመተመን የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ከላይ የተዘረዘሩት ሲሆኑ ከታሰበዉ በላይ የተገኘ ገቢ (Excess Earnings) ዘዴ፣ የተገኘ ተጨማሪ ትርፍ (Premium Profit) ዘዴ እና ሌሎች የተለያዩ የአእምሯዊ ንብረት ትመና ዘዴዎችም አሉ፡፡
በኢትዮጵያ የፈጠራ ባለሙያዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ቀዳሚው የፈጠራ ስራዎቻቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚውል የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የዜጎችን በፋይናንስ ስርዐቱ እኩል ተጠቃሚነት ለማጎልበት ታስቦ የፀደቀው ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በመያዣነት በመጠቀም የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ ቁጥር 1147/2012 በብሄራዊ ባንክ የፀደቀ ሲሆን በዚህ አዋጅ ተንቀሳቃሽ ንብረት ተብለው ከተመደቡት መካከል የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ይገኙበታል፡፡ ስለሆነም ይህ አዋጅ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች እንደ መያዣ በመጠቀም የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችና የፈጠራ ስራ ባለሙያዎች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እና የሰሯቸውን ስራዎች ለሰፊው ማኅበረሰብ እንዲያደርሱ፣ ተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያፈልቁ፣ የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንዲያስፋፉ እና የስራ ፈጠራን በማበረታታት እንደ አጠቃላይ በሃገር ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ሊያስገኝ ይችላል፡፡
ይህ እንዲሳካ ደግሞ ቀልጣፋ፣ተደራሽና ጥራት ያለው የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባ ስርዓት እንዲኖር መስራት፣ በባንኮች፣ኢንሹራንሶች እና የፋይናንስ ተቋማት ያሉ ባለሙያዎች ስለ አእምሯዊ ንብረት ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እና የአእምሯዊ ንብረቶች ትመናን ተገቢውን የትመና ዘዴ እና ጥንቃቄ በማድረግ በመከወን የፋይናንስ ስርዐቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ማድረግ ይቻላል፡፡