የጽ/ቤቱ ማኔጅመንት ኮሚቴ ዓባላትና የየክፍሉ የቡድን መሪዎች የ2012 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ሐምሌ 17/2012 ዓ.ም በጽ/ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ገመገሙ፡፡ በግምገማው ወቅት ተቋሙ በ2020 ዓ.ም አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ ለማድረግ አቅዷል፤ በዚህም የጽ/ቤቱ ኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ያለውን የስራ መነቃቃት በመጠቀም የበለጠ ዕገዛ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ስራውን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በሪፖርት ግምገማው ላይ የተገኙት የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኤርምያስ የማነብርሃን የቀረቡት አብዛኞቹ ሪፖርቶች ከሞላ ጎደል ጥሩ ናቸው፤ ነገር ግን ከልማዳዊ አሰራር ወጥተን አዳዲስ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡ በቀጣይ በጀት ዓመት ጽ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን ስራዎች ዘርዝረው በዋናነት በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ በመስራት እሴት በመጨመር እና ጥራቱ ላይ ትኩረት በመስጠት ተወዳዳሪ መሆን የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፤ብለዋል፡፡ ይህን ለማሰካት ደግሞ ብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት የመረጃ ማዕከል በማቋቋም እና በጣም የታወቁ የሀገራችንን ምርቶች ወደ ብራንድነት በመቀየር አርሶአደሩ ምርቱን ወደ ንግድ እንዲያደርስ ታቅዶ መሰራት እንዳለበት አጽንዖት በመስጠት አብራርተዋል፡፡