የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት አገልግሎቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችለውን አሰራር ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት /WIPO/ ጋር በመተባበር የኢንዱስትሪያዊ ንብረት አሰተዳደር /IPAS/ እና /WIPO file/ ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
ይህ አሰራር የምዝገባ ሂደቶች ዲጅታይዝድ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ የኦን ላይን አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ አስችሏል፡፡
ይህንን የኤሌክትሮኒክ ፋይል ስርዓት በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችም ጭምር ተግባራዊ በማድረግ የወረዳ ኔት ስርዓትን በመጠቀም የሚሰጡ አገልግሎቶች የተሟሉ እንዲሆኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት የማሻሻልና የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ በዚህም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንደ ዋናው ጽ/ቤት ሁሉ የማመልከቻ ቅበላና ተያያዥ አገልግሎቶችን በተለይ ለንግድ ምልክት ምዝገባ ማመልከቻ ደንበኞች በአካል ሳይቀርቡ በኦን ላይን ማመልከት እንዲችሉ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጽ/ቤቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የንግድ ምልክት ጥበቃና ልማት ባለሙያዎች በሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመገኘት የሙያዊ ድጋፍና የሠራተኞች ሥልጠና አካሂደዋል፡፡