በቅጅ መብት ሕግ የስነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ሰዓሊያንና ቀራፂያን እንደ ደራሲያንና ሙዚቀኞች በቅጅ ስራዎች (በድጋሚ ምርት) እና በተግባቦት መብቶች የሚገኙ ጥቅሞች ተጋሪ አይደሉም፡፡ ይህም የስነ ጥበብ ስራ አመንጪዎች በህብረተሰቡ ዕውቅና ከማግኘታቸው በፊት ሥራዎቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ ነበር፡፡ ይሁንና የስነ-ጥበብ ስራ አመንጪዎች በህብረተሰቡ ዘንድ መልካም ዝናን ካተረፉ በኋላ ቀደም ብለው ስራዎቻቸውን የገዙት ሰዎች ከባለመብቶቹ ከገዙበት ዋጋ በከፍተኛ ብልጫ በመሸጥ ትልቅ ትርፍ ያገኙበታል፡፡ ነገር ግን የስነ-ጥበብ ስራ አመንጪዎቹ ከዚህ አይነቱ የድጋሚ ሽያጭ ከሚገኝ ትርፍ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ በመሆኑም የድጋሚ ሽያጭ የሮያሊቲ መብት ወይም በአውሮፓ በሰፊው የሚታወቅበት “ዶሪ ደሱ” የስነጥበብ ስራ አመንጪዎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘረጋ ስርዓት ነው፡፡
የድጋሚ ሽያጭ ያስፈለገበት የስነ-ጥበብ ስራዎች ተፈላጊነት በአያሌው ሲጨምር አዳዲስ የግብይት ሰንሰለቶች ይፈጠራሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የስነ-ጥበብ የጨረታ ቤቶች፣ የንግድ ጋለሪዎችና የስነ-ጥበብ ትዕይንት ማሳያዎች እና የመሳሰሉ ተቋማት በገዟቸው የስነ-ጥበብ ስራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል የስራ አመንጪዎቹ የድጋሚ ሽያጭ ጥቅም ተጋሪ ባለመሆናቸው የጥበብ ስራዎቻቸው የሶስተኛ ወገኖችን የገቢ ምንጭ በአያሌው ሲያሳድግ እነርሱ ግን ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እንዲመሩ ይገደዳሉ፡፡ ለዚህም ዋና ማሳያ የሚሆነው ፈረንሳዊው የቅብ ባለሙያ ጄን ፋራንኮይስ ማሌት “ዘአንጀሉስ” የተባለ ሥራውን በዝቅተኛ ዋጋ ከሸጠው ከዓመታት በኋላ የስነ-ጥበብ ስራው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ በድጋሚ ተሸጧል፡፡ ይህም የስነ-ጥበብ ስራው አመንጪውን ተጠቃሚ ባለማድረጉ እሱንና ቤተሰቡን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡ ስለሆነም የድጋሚ ሽያጭ ስርዓት በስነ-ጥበብ ስራ አመንጪዎች ላይ የሚደርሰውን ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለመቅረፍ ታሳቢ በማድረግ እ.አ.አ በ1920 በፈረንሳይ ሀገር የድጋሚ ሽያጭ ሕግ እንዲወጣ ተደረገ፡፡
የ1948ቱ የበርን ስነ-ጽሑፍና የኪነ-ጥበብ ስምምነት የድጋሚ ሽያጭ መብትን የተመለከተ አንቀጽ በማካተት አባል ሀገራት በፍቃደኝነት የድጋሚ ሽያጭ መብት ሕግ ሊያወጡ እንደሚችሉ ይገልፃል፡፡ (በዚህም ከድጋሚ ሽያጭ መብት ሮያሊቲ ለመሰብሰብ የግብይቱ ወገኖች /ገዥ እና ሻጭ/ ሀገሮቻቸው የድጋሚ ሽያጭ መብት ሕግ ያወጡ እንደሆነ ነው፡፡) ይህም የሚሆነው ከድጋሚ ሽያጭ መብት ሮያሊቲ ለመሰብሰብ የግብይቱ ተሳታፊ ሀገሮች የድጋሚ ሽያጭ መብትን የሚያስጠብቅ ሕግ የሚደነግጉ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
በበርን ስምምነት ወጥ የስነ-ጥበብ ስራዎች (original works of art) እና ወጥ የስነ-ጽሑፍ ስራዎች (original works of writer) የሙዚቃ ቅንብሮች (composers’ works) በሽያጭ ከተላለፉ በኋላ የስራ አመንጪዎች፤ የስራ አመንጪዎች በሕይወት የሌሉ እንደሆነ ወራሾች የተወሰነ ድርሻ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡ በመሆኑም የሥራ አመንጪዎች መብት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የስምምነቱ አባል ሀገራት በሕጎቻቸው ሲያካትቱ ነው፡፡ የአሰባሰቡና የክፍያ መጠኑን በተመለከተ ሀገራት በሚያወጡት ደንብ የሚወሰን ይሆናል፡፡በሀገራችን ወጥነት ያለው የስነ-ጥበብ፣ የስነ-ጽሁፍና የሙዚቃ ስራዎች ከድጋሚ ሽያጭ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በስራ አመንጪዎችና በድጋሚ ሽያጩ የሚሳተፉ ሰዎች መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤ እንዲሁም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 7 (3) የአንድ ወጥ የስነ-ጥበብ ስራ ወይም የአንድ ደራሲ ወይንም የዜማ ደራሲ ኦሪጅናል ጽሁፍ ከስራ አመንጪው ለሁለተኛ ሰው ከተላለፈ፤ከሚደረገው የድጋሚ ሽያጭ ዋጋ ላይ የስራ አመንጪው ወይም ወራሹ የተወሰነ ድርሻ የማግኘት መብት እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በብዙ ሀገራት እየተሰራበት ያለው የድጋሚ ሽያጭ መብት፤ የስነ-ጥበብ ንግድ ሥራ በሚሰሩ (art market professionals) ማለትም በስነ-ጥበብ ስራ አሻሻጮች (auctioneer)፣ “በጋለሪ” ባለቤቶች (ተወካይ)፣ እና በሙዚየም ባለቤቶች (ተወካይ) አማካኝነት የስነ-ጥበብ ሥራው በድጋሚ ሲሸጥ የሥራው አመንጪ ወይም ወራሹ ከሽያጩ የተወሰነ “ፐርሰንት” ወይም ሮያሊቲ የሚያስገኝ መብት ነው፡፡ የድጋሚ ሽያጭ መብት ዓላማ የሥራ አመንጪው ወይም ወራሾቹ ከድጋሚ ሽያጩ ከሚያገኘው ከፍተኛ ትርፍ የተወሰነ ድርሻ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
የድጋሚ ሽያጭ መብት ተግባራዊ የሚሆንባቸው የስራ ምድቦች የሶስት ሀገራት ተሞክሮን እንመልከት፡፡
በመጀመሪያ በአውስትራሊያ፡ በድጋሚ ሽያጭ የሚታቀፉ የሥራ አይነቶች ወጥ የስነ-ጥበብ ሥራዎች ስነ-ስዕል፣ የፎቶግራፍ ስራ፣ የህትመት ስራ፣ የቅርጻ ቅርጽ ስራ፣ ጥልፍ፣ ዲዛይንን ያካተተ የሽመና ስራ፣ የተንቀሳቃሽ ምስል ስራ (video art works) ፣ የጨርቃ ጨርቅ ጥበብ ስራዎች (textile art works) ፣ ሽመና (weaving)፣ ጌጣጌጥ፣ የመስታዎት ላይ ስራ “ግላስዌር”፣ “ግሬቪንግ”፣ ሴራሚክስ ዲጂታልና የመልቲሚዲያ ስራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ስራዎች የሥራ አመንጪው ከሞተ 70 ዓመት በኋላ ተፈፃሚ አይሆኑም፡፡ እንዲሁም በብዛት በሚመረቱ “ፖስተሮች” ወይም “ሱቪኒየሮች”፣ ህንፃዎች፣ “የአርክቴክት” ፕላኖች፣ “ሰርኪውት ሌይአውት” ወይም “ማኑስክሪፕቶች” አይካተቱም፡፡
ሁለተኛ በካናዳ፡ የቅጅ መብት ሕግ የድጋሚ ሽያጭ መብት ከሚያስገኙ የስነ-ጥበብ ስራዎች መካከል የቅብ፣ የንድፍ፣ የህትመት፣ ቅርፃቅርፅ የእጅ ሥራዎችና የስነ-ጥበብ ስብስቦች የተካተቱ ቢሆንም “ማፕ”፣ “ቻርት”፣ “ፕላን” እና “የአርክቴክቸር” ሥራዎች ግን ሊካተቱ አልቻሉም፡፡
ሶስተኛ በእንግሊዝ፡ የድጋሚ ሽያጭ መብት በጨረታ ቤቶች (auction house) በጋለሪዎችና (art gallery) በአሻሻጮች (art dealers) አማካኝነት መካሄድ ይኖርበታል፡፡የድጋሚ ሽያጭ ሮያሊቲ አሰባሰብና አከፋፈል በጋራ አስተዳደር ማህበር አማካኝነት የሚከናወን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በግለሰቦች መካከል የሚካሄድ ግብይት የድጋሚ ሽያጭ መብትን አይመለከትም፡፡
በሀገራችን የድጋሚ ሽያጭ መብት በሶስት የስራ ምድቦች ሽፋን ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡ እነዚህም ወጥነት ያለው ስነ-ጽሁፍ (original manuscripts of work) ፣የሙዚቃ ቅንብር (original works of composer) እና የስነ-ጥበብ ስራዎች ናቸው፡፡
መጽሐፍ፣”ቡክሌት”፣በመጽሔት ወይም በጋዜጣ ላይ የሚገኝ መጣጥፍ፣ የኮምፒውተር ፕሮግራም፣ንግግር፣”ሌክቸር”፣ ለአንድ የተወሰነ ክፍል የሚደረግ መልዕክት፣ መልዕክት አዘል ንግግር፣ የሀይማኖት ስብከት፣ በቃል የቀረበ ስራ እና የዕደ-ጥበብ ስራዎች፣ በወጥ ስነ-ጽሑፎች (original manuscripts of works) እንዲሁም ወጥ የሙዚቃ ቅንብር (original works of composer)፤ በተጨማሪም የንድፍ፣ የሥዕል፣ የቅብ፣ የሀውልት፣ የቅርፃቅርፅ፣ የፊደልና ሌላ ወጥ የስነ-ጥበብ ሥራዎች በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁጥር 410/1996 የተካተቱ ናቸው፡፡
ምንም እንኳን የስነ-ጽሑፍና የሙዚቃ ስራ አመንጪዎች ስራውን በማባዛት በሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ ቢሆኑም ከስነ-ጥበብ ስራ አመንጪዎች ተርታ እንዲታዩ የሚስተናገዱበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው “ኦርጅናል” (ወጥ) ሥራዎቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ በመሆናቸው ነው፡፡
የድጋሚ ሽያጭ መብት አስተዳደር በተናጠል ወይም በቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር አማካኝነት ሊከናወን ይችላል፡፡ በአብዛኛው የተለመደውና ቀልጣፋ አስተዳደር የሚሰጠው በጋራ አስተዳደር ማህበራት አማካኝነት ነው፡፡ በተጨማሪም መሸጫ ሱቆች፣ ጋለሪና ሙዚየሞች ለጋራ አስተዳደር ማህበራት መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን የአውሮፓ ህብረት “ዳይሬክቲቭ” የድጋሚ ሽያጭ መብት አስተዳደር ስራን ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ አስተዳደር ማህበራትን ማቋቋም ግዴታ አላደረገውም፡፡
ስለሆነም የድጋሚ ሽያጭ መብት ህግን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገሮችን መልካም ተሞክሮ መዳሰስ እና የሀገራችንን የስራ አመንጪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ለማበጀት ባለድርሻዎችን በማሳተፍና የድጋሚ ሽያጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በማጥናት ደንብ የማዘጋጀት ተግባር በቀጣይ የሚተኮርበት ይሆናል፡፡
በኮፒራይትና ማህበረሰቦች ዕውቀት ጥበቃና ልማት ዳይሬክቶሬት እና በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
ምንጭ፡- የድጋሚ ሽያጭ መብት /የደሰሳ ጥናት/