“IP and the SDGs: Building our common future with innovation and creativity”
አእምሯዊ ንብረት ለዘላቂ ልማት፡ መጪው ጊዜያችንን በኢኖቬሽንና ፈጠራ እንገንባ! በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው የአእምሯዊ ንብረት ቀን በሳይንስ ሙዚየም ዛሬ ሚያዝያ 18፣ 2016 ዓ.ም በደማቅ ዝግጅት ተከብሯል፡፡ በሁነቱ የፓናል ውይይትና የፈጠራ ስራዎች አውደ-ርዕይ ተካሄዷል፡፡
በዓሉን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ወልዱ ይመሰል እንደ ፓተንት፣ የንግድ ምልክቶች/ብራንዶች/፣ ኢንዱስትሪያዊ ዲዛይን፣ ሶፍትዌርና ተያያዥ የፈጠራ ውጤቶች የሃገራት የኢኮኖሚ መሰረት የሆኑበት ዘመን ላይ እንገኛለን፤ ስለዚህም ይህንን ለውጥ ለመገንዘብ እና ለመጠቀም ጠንካራ የአእምሯዊ ንብረት ፖሊሲ፤ ስትራቴጂ፤ የህግ ማእቀፍና ተuማዊ አቅም መገንባት ወሳኝ ሆል ብለዋል፡፡ በበዓሉ መሪ ሃሳብ መነሻነትም የአእምሯዊ ንብረት ዘርፍ ለሃገር ዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት አስተዋጽኦው እንዲያድግ ዘርፉን በይበልጥ መደገፍ ይገባል ሲሉ አክለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ክቡር ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በሀገራችን የኢኖቬሽንና ስታርታፕ ሃሳቦችን ውጤታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሽጋገር እንዲቻል የስታርትፕ መሠረት የሆኑት የፈጠራ ስራዎችና የቢዝነስ ሃሳቦች በአእምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ የፈጠራ አመንጪዎችን ሕጋዊ ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእጅጉ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ወንድወሰን በለጠ የአእምሯዊ ንብረት አማካሪ “The Role of IP for Development and Technology Transfer”፤ ዶ/ር ሀብታሙ አበራ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ምርምርና ስርጸት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ “The Role of IP for Research and Development”፤ ዶ/ር ትዕግስት ደሱ የካፒታል ቢዝነስ ትምህርት ቤት ዲይሬክተር እና በኢትዮ አልያንስ አድቮኬት ከፍተኛ የአእምሯዊ ንብረት አማካሪ እንዲሁም ቃለእግዚአብሄር ጎሳዬ ከኢትዮ አልያንስ አድቮኬት “Implementing SDGs in the National IP system፡ the dilemma of TM on Ethiopian Coffee versus GI” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽሁፍ አቅርበው በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን እና የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት አካዳሚ አማካሪ ብሩክ ኃይሌ (ዶ/ር) የተመራ ውይይት ተካዷል፡፡
በዚህ ዓለም አቀፋዊና ሃገራዊ በዓል ፈጠራና ኢኖቬሽን ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ለማስገንዘብ እና የፈጠራ ባህልን ለማጎልበት፣ ሃገር በቀል ፈጠራን ለማበረታታት ብሎም የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ዘርፍን ለማሳደግ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡