የኢትዮጵያ ፊልም ኢንድስትሪ ባለመብቶችንና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ፋይን አርትስና ዲዛይን ኮሌጅ የፊልም ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል እና በመልቲቾይስ /ዲኤስቲቪ ኢትዮጵያ የጋራ ትብብር  “ትብብር ለፊልም ቅጅና ተዛማጅ መብቶች” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማዘመንና የባለመብቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የዘርፉ ባለሙያዎችና  ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት ዓለም በምትመራበት በእውቀት መር ኢኮኖሚ ውስጥ የሀገራችንን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥና የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል የአእምሯዊ ንብረት ዘርፍን የእድገት አንቀሳቃሽ መሳሪያ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኮፒራይት ኢንዱስትሪ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ባህላዊ እድገት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሲሰጠውና በዘርፉ የተሰማሩ የፈጠራ ባለመብቶች ከሥራዎቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚበረታቱበትን ስርዓት  መፍጠር ሲቻል እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

በተለይ የፊልም ኢንዱስትሪው በርከት ያለ የስራ እድል በመፍጠር፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማፋጠን፣ ባህል በማስተዋወቅና የውጪ ኢንቨስትመት በመሳብ ረገድ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የኢንዱስትሪውን ዕድገት በማነቃቃት ባለመብቱን ብሎም ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ የባለመብቱን፣ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅታዊ ስራን በእጅጉ እንደሚሻ አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ፋይን አርትስና ዲዛይን ኮሌጅ የፊልም ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ታዲዮስ ጌታቸው በመሩት በዚህ መድረክ ላይ የቅጅ መብት ጽንስ ሃሳብ፣ የፊልም ኢንዱስትሪው እድሎችና ተግዳሮቶች፣ የፊልም ኢንዱስትሪ ተዋናይ መብቶች በተመለከተ በፓናሊስቶች ውይይት ተደርጓል፡፡

የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያንቀሳቅሰው የሰው ኃይልና ፋይናንስ ከፍተኛ ቢሆንም ለሀገራዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ባለመብቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ  አስተዋጽኦ እምብዛም እንደሆነ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የፊልም ኢንዱስትሪው ለባለመብቶችና ለሀገራዊ ዕድገት ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ፤ የባለመብቶችንና የህዝቡን ግንዛቤ ማስፋት፣ የህግ ተፈጻሚነትን ማሳደግ፣ በፍርድ ቤቶች የአእምሯዊ ንብረት ጉዳይ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኝ ስርዓት መፍጠር፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃን ያማከለ የመብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እና በኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ የመብት ገሰሳዎችን ለመቀነስ የወንጀልና የፍትሐብሔር ተጠያቂነትን ማሳደግ እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS