የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና የአሶሳ ዩንቨርስቲ መግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

በአእምሯዊ ንብረት ምንነት፣ የፓተንት ስርዓት በኢትዮጵያ፤ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ድጋፍ ማዕከላት፣ በተግባር የታገዘ የፓተንት መረጃ አፈላለግ እንዲሁም ተቋማዊ የአእምሯዊ ንብረት ፖሊስን በተመለከተ ከየካቲት 10-12/2014 ዓ.ም. በአሶሳ ዩንቨርስቲ ስልጠና ተካሄደ:: በስልጠናው የዩንቨርስቲው መምህራንና ሰራተኞች፣ የፈጠራ ሰራተኞች፣ ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ ከተለያዩ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የተወጣጡ ተሳታፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከስልጠናው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና የአሶሳ ዩንቨርስቲ በፓተንት መረጃ፣ በአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ሌሎች ከአእምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዙ ጉዳዩች ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት የካቲት 11/2014 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው ሞሲሳ እና የአሶሳ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ናቸው፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አእምሯዊ ንብረትን እንደ ልማት መሳሪያነት በመጠቀም አሁን አለም ያለችበትን የእውቀት መር ኢኮኖሚ ሃገራችን በፍጥነት መቀላቀል እንድትችል የዩንቨርስቲዎች፣ የምርምር እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ይህንን የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በማድረግ ከዩንቨርስቲው ጋር በቅርበት የሚሰሩ መሆኑን እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን በመመደብ አስፈላጊውን ሁሉ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው፤ ይህንን ስልጠና እና የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም ላመቻቹ የዩንቨርስቲው ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በስልጠናው ላይ በተዳሰሱ ርእሶች ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎች ስልጠናው በየተቋማቱ የተሰሩ ፈጠራዎችን በተለያዩ የአእምሯዊ ንብረት ዘርፎች መብት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ አሰራሮች ላይ አቅም የሚፈጥር መሆኑን እና በየተቋማቱ የተሰሩ ፈጠራዎችን እንዴት ወደ ህብረተሰቡ መሸጋገር እንዳለባቸው የሚያሳውቁ የህግና የአሰራር ስርዓቶችን እንዲገነዘቡ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የዩንቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሃይማኖት ዲሳሳ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎችን ማስመዝገብ ላይ እንዲሁም ተቋማዊ አእምሯዊ ንብረት ፖሊሲ አለመኖር ግልጽ እና በአሰራር ስርዓት የተደገፈ የቴክኖሎጂ ሸግግር እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ እንዳይቻል ክፍተት የሚፈጥር በመሆኑ በዩንቨርስቲው ተቋማዊ አእምሯዊ ንብረት ፖሊሲ እንዲኖር ስራዎች የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የዩንቨርስቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታቸው አለሙ የአእምሯዊ ንብረት ባለመብትነት ማግኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእውቀትና ፈጠራ አመንጪዎች እውቅና እና የብቸኝነት መብት መስጠቱ ካሉት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ባሻገር የፈጠራ ሰራተኞች ባፈለቋቸው ስራዎች የፈጠራ ሰራተኛ ወይም የስራዎቹ አመንጪ መሆናቸው መረጋገጡ በራሱ ከፍተኛ የሆነ የሞራል መነቃቃትን የሚፈጥርና ለአዳዲስ ፈጠራዎች የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዩንቨርስቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በተለያየ መስክ እውቀትና ልምድ ያለው የሰው ሃይልን እንደ ሃብት በመቁጠር የህረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ቴክሎጂዎችን በማፍለቅ እና በማሸጋገር ላይ በቅንጅት በመስራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፈነታቸውን እንዲወጡ ዶ/ር ጌታቸው አሳስበዋል፡፡

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS