የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ! አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የኢኖቬሽን ሥርዓት ግንባታ

በወንድወሰን በለጠ

በዓለም ዓቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆንና ዘለቄታዊ ልማትን ለማረጋገጥ ሀገራት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ኢኖቬሽን ቁልፍ ድርሻ አለው፡፡ መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች የሆኑትን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የጤና አገልግሎት ፣ የምግብ አቅርቦት የመሳሰሉትን ለማሳካትም የኢኖቬሽን አቅምን መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ ኢኖቬሽን ነባር ምርቶችንና አገልግሎቶችን በተሻለ ሁኔታ ማቅረብን ከማስቻሉ ባሻገር አዳዲስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ ስለሚረዳ የሰዎችን ምርጫ በማስፋት ረገድም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

ኢኖቬሽን የተለያዩ ተዋንያንና ተቋማት የእርስ በርስ መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ የነዚህ ተዋንያንና ተቋማት የርስ በርስ ትስስር የሚፈጥረው ሥርዓት የኢኖቬሽንን ውጤታማነት ይወስናል፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂ ልማትን በማረጋገጥ የሀገራትን የእድገት ሒደት ለማፋጠን ተቋማትን ማጠናከርና የተዋንያኑን አቅም መገንባት እንዲሁም በመካከላቸው ያለውን ትስስር የተሳለጠ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የተጠናከረ የኢኖቬሽን ስርአት መፈጠር ለኤኮኖሚያዊ ልማት መሰረት ነው፡፡

የኢኖቬሽን ሥርዓት የተለያዩ በቴክኖሎጂ እድገት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አስቻይ ሁኔታዎችን ያካተተ ሲሆን ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ሁኔታዎችንም ይይዛል፡፡ ይህም የሚያሳየው አንድ ሀገር በኢኖቬሽን ላይ የተመሰረተ ኤኮኖሚያዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ዘርፈ ብዙ ገፅታ ያለውና መጠነ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴን  የሚጠይቅ ነው፡፡

ብሔራዊ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እና ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት የሚደረግ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ፖሊሲ አውጪዎች ስለ ብሔራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ አለመጣጣሞችን በመለየት ተቋማትን ማጠናከርና አግባብ ያላቸው ፖሊሲዎችን ማውጣት እና  መተግበር ይቻላል፡፡የኢኖቬሽን ፖሊሲ መሳሪያዎች በቴክኖሎጂ ልማት ላይ የሚያተኩሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በቴክኖሎጂ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን መጣጣም ለማረጋገጥ የሚረዱ እና ሌሎች ማዕቀፎችን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ማዕቀፎች የሚይዙት የፋይናንስ አቅርቦት፣ የታክስና የማበረታቻ ሁኔታን፣ የኢኖቬሽን ዝንባሌንና አንተርፕረነርሺፕን ነው፡፡ ሌሎች በኢኖቬሽን ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ የሚኖራቸው ተቋማዊ ሁኔታዎች የምርትና የአገልግሎት ደረጃዎችን የሚወስኑ ሕጎች ፣ የአእምሯዊ ንበረት ጥበቃ ሥርዓት፣ ቬንቸር ካፒታልና ሌሎች የቢዝነስ ድጋፍ ሥርዓት አካላት ናቸው፡፡

በብሔራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓት ውስጥ ካሉ ቁልፍ ተዋንያን መካከል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበትና በየዘርፋቸው የቴክኖሎጂ ልማትን ለማፋጠን የሚኖራቸው እገዛ ላቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ የኢኖቬሽን ሥርዓት ውጤታማነት መገለጫ በኢንተርፕራይዞች እና በሌሎች የኢኖቬሽን ተዋንያን መካከል ጥብቅ ትስስር መኖሩ ነው፡፡ እነዚህ ሌሎች የኢኖቬሽን ሥርዓት ተዋንያን ዩኒቨርስቲዎችን ፣ የመንግሥት የምርምር ተቋማትንና ትላልቅ የሀገር ውስጥ ዓለም አቀፍ ኢንተርፕራይዞችን እንዲሁም ድንበር ዘለል ኩባንያዎችን ያካትታሉ፡፡

በዩኒቨርስቲዎችና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያለው ትስስር መጠናከር፤ የኢንተርፕራይዞችን የኢኖቬሽን አቅም ከፍ ለማድረግ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ከማስተማርና ከምርምር ጋር ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢ ማኅበረሰብ ዕድገትና ልማት ላይ ያተኮረ ሥራ መስራት ተቋማቱ ከኢንተርፕራይዞች ጋር እንዲተሳሰሩና የኢንተርፕረነርሺፕ ሥራን እንዲያከናውኑ ያግዛቸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎችና ኢንተርፕራይዞች ሊተባበሩና ቅንጅት ሊፈጥሩ የሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ በላይሰንስ ሥምምነቶች አማካነት የሚደረግ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የምክር አገልግሎቶች፣ የጋራ ፕሮጀክቶች ትግበራና የአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ምሥረታ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር መንገዶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህን መሠል ተግባራት የኢንተርፕራይዞችን የኢኖቬሽን ብቃት ደረጃ የሚያሳድጉና የተወዳዳሪነት አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ናቸው፡፡ በዩኒቨርስቲዎች የሚሰጥ ሥልጠናና የሰው ኃይል አቅርቦትም ሌላው የኢንተርፕራይዞች ቴክኖሎጂን የመጠቀምና የማሻሻል አቅም ከፍ የሚልበት መንገድ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በበቂ መጠን ሲኖራቸው የውጪ ቴክኖሎጂና እውቀት የመጠቀም እንዲሁም ቴክኖሎጂን የማመንጨት አቅማቸው ይዳብራል፡፡

የመንግሥት የምርምር ድርጅቶች ሌሎቹ ከኢንተርፕራይዞች ጋር ትስስር ሊኖራቸው የሚገባ የኢኖሼሽን ሥርዓት ተዋንያን ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥ የምርትና የአገልግሎት ተቋማትን በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ በመንግሥት የምርምር ድርጅቶች ተልዕኮ ውስጥ ይካተታል፡፡ በአብዛኛው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋምና የነባሮችን አቅም በማሳደግ ሒደት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ የኢንተርፕራይዞችን የቴክኖሎጂ ችግሮች መሠረት ያደረጉ የምርምር ተግባራትን በማከናወን ለእንቅስቃሴያቸው መሳለጥም ዓይነተኛ አስተዋፅዖን ያበረክታሉ፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይች ከትልልቅ ኢንተርፕራይዞች ጋር የሚፈጥሩት መስተጋብር ሌላው በኢኖቬሽን ልማት ሂደት ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው ጉይይ ነው፡፡ ከሀገር ውስጥ ትልልቅ ኢንተርፕራይዞች በተጨማሪም የድንበር ዘለል ኩባንያዎች ከአነስተኛና መካለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ እየተጠናከረ በመሔድ ላይ በሚገኘው የሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ምክንያት በርካታ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች የምርት ሒደቶቻቸውን በታዳጊ ሀገራት የሚያከናውኑበት ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በዚህም ሒደት አነስተ”ና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሁኔታ ለእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር አመቺ ሁኔታን በመፍጠር የታዳጊ ሀገራትን አቅም ያዳብራል፡፡

በብሔራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓት ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከሌሎች የኢኖቬሽን ተዋንያን ጋር በሚፈጥሩት ትስስር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ተቋማዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡ መደበኛና ኢመደበኛ የሆኑ ሕጎች ፣ ደንቦች አሠራሮች እንዲሁም ሒደቶች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከነዚህ ተቋማዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ነው፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከሌሎች የኢኖቬሽን ሥርዓት አካላት ጋር በጋራ በሚያከናውኗቸው ተግባራት በሚገኙ ውጤቶች ላይ የአእምሯዊ ንብረት መብቶቻቸው የሚረጋግጡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ከዚህም በተጨማሪ የነሱን የአእምሮ ሥራ ውጤቶች ሌሎች የኢኖቬሽን ሥርዓቱ ተዋናዮች ሲጠቀሙ መብቶቻቸውን ባከበረ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡በሌላ መልኩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ ልማት ተግባራትን ሲያከናውኑ የሶስተኛ ወገኖችን የአእምሯዊ ንብረት መብት በሚጥስ ሁኔታ መሆን የለበትም፡፡የአእምሯዊ ንብረት ሕጎችን አክብረው የሚንቀሳቀሱ ኢንተርፕራይዞች የሕግ ጥሰት ተጠያቂነትን በማስቀረት አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስና ውጤታማ ቴክኖሎጂያዊ እንቅስቃሴን ማድረግ ይችላሉ፡፡

ሌላው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከአእምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዘ የሚያገኙት ጠቀሜታ፤ ከኢንቨስተሮች ፣ በሽርክና ሊሰሩ ከሚችሉ አካላት፣ ከተፎካካሪዎችና ከተጠቃሚዎች ጋር የሰመረ ግንኙነት መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ኢንተርፕራይዞች በአበዳሪ ተgማት እይታ የሚኖራቸው ዋጋ ከፍ እንዲልም አእምሯዊ ንብረት የጎላ አስተዋፅዖ ያለው ሲሆን ገበያቸውን በማሳደግም በኩል ትልቅ ድርሻ ይይዛል፡፡

የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ዋና አላማ ተቋማትና ግለሰቦች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨት ከሚያወጡት ቁሳዊ ሀብት፣ ከሚጠቀሙት ዕውቀትና ጊዜ አትራፊ እንዲሆኑ በማስቻል በቀጣይ የሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂ አመንጪዎችን ተነሳሽነት በማሳደግና የኢንተርፕረነርሺፕ መንፈስን በማጐልበት ልማትን ማፋጠን ነው፡፡

ውጤታማ የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በገበያ ውስጥ ያላቸውን ተወዳዳሪነትና ስትራቴያጂየዊ ብቃትም ያጎለብታል፡፡ ምንም እንኳን የኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነት የሚወስኑ በርካታ ሁኔታዎች ያሉ ቢሆንም አእምሯዊ ንብረትን በአግባቡ መጠቀም ለገበያ ስኬታማነት መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የቴክኖሎጂ አመንጪዎችና የቴከኖሎጂ ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ያመጣጠነ የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት መኖርና በስፋት ጥቅም ላይ መዋል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚፈልጉትን ቴክኖሎጂ በተመጣጣ– ወጪ አንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በማሻሻል ሂደት ኢንተርፕራይዞቹ ለሚያመነጩት አዲስ ቴክኖሎጂ የባለቤትነት መብትን በማረጋገጥ ተጠቃሚነታቸውን ያሳድጋል፡፡

የአእምሯዊ ንብረት መብት ባለቤትነትን ማረጋገጫ ማግ‘ት የመጀመሪውና ወሳኙ ርምጃ ቢሆንም ውጤታማ የአእምሯዊ ንብረት አስተዳደር ፈጠራን፣ የንግድ ምልክትን እና የቅጅ መብትን ከማስጠበቅ ያለፈ ነው፡፡ ዕውቀትን ሶሰተኛ ወገኖች በፈቃድ ሥምምነት ላይ ተመስርተው እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ ስትራቴጂያዊ ሽርክናዎችን ማስፋት ፣ እንዲሁም የመብት ጥሰቶችን መከታተልና ሕጋዊ ተፈፃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መሥራት ኢንተርፕራየዞች ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ባለፉት ጥቲት ዓመታት በርካታ በመልማት ላይ ያሉ ሀገራት የኢኖቬሽን ሥርዓትን መሠረት ያደረጉ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲዎችን አውጥተዋል፡፡ከነዚህ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ብሔራዊ የኢኖቬሽን ሥርዓትን በመገንባት ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ልማትን ማረጋገጥ አንዱ ዋነኛ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ በመውሰድ ሀገሪቱ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በልማት ዕቅዶችና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲዋ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ሕጎችና ደንቦች ውስጥም አንዲንፀባረቅ ተደርጓል፡፡

ሀገሪቱ የብሔራዊ ኢኖቬሽን ሥርዓት ግንባታን እንደዋነኛ ስትራቴጂ መውሰዷ ትልቅ ርምጃ ቢሆንም በኢኖቬሽን ተዋንያኑ መካከል ያለው ግንኙነት ያልተቀናጀና ደካማ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲዎች ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማሰልጠን የኢንተርፕራይዞችን ፍላጎት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዩኒቨርስቲዎች ተመርቆ በሚወጣው የሰው ኃይል ዕውቀትና ክህሎት በኢንተርፕራይዞች ፍላጎት መካከል ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲዎች ኢኮኖሚውን መሠረት ያደረጉ የምርምር ተግባራትን በማከናወን ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ወደ ኢንተርፕራይዞች በስፋት ማሸጋገር አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድም ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ ተግባር ሲከናወንና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታይም ፡፡ የዩኒቨርስቲዎች የምርምር ተግባራት ውስን ከመሆኑ በተጨማሪ በኢንተርፕራይዞቹ የቴክኖሎጂ ፍላጎትና በዩኒቨርስቲዎች ምርምር መካከል ሰፊ ያለመጣጣም ይታያል፡፡ በመሆኑም የዩኒቨርስቲዎች የስልጠናና ምርምር ተግባራት ለኢንተርፕራይዞች ልማት እያበረቱ ያለው አስተዋፅኦ አናሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከመንግሥት የምርምር ድርጅቶች በሚያገኙት ድጋፍ በኩልም የጎላ ችግር ይታያል፡፡ በሀገሪቱ እንደግብርናና ጤናው ዘርፎች የተጠናከረ የምርምር ሥራ በኢንዱስትሪው ዘርፍ አይታይም፡፡ በአንዳንድ ዘርፎች የተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ልማት ተቋማት ያሉ ቢሆንም ከኢንተርፕራይዞቹ ጋር ያላቸው ትስስር ደካማ ነው፡፡ ይህ በዩኒቨርስቲዎች፣ በመንግሥት የምርምር ድርጅቶችና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያለ ደካማ ትስስር በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በዚህም የተነሣ ኢንተርፕራይዞቹ በተፈላጊው ዓይነትና መጠን አዳዲስና የተሻሻሉ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት የምርምር ተgማት ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር ያላቸው ትስስር ደካማ መሆኑ በእውቀት አመንጪ ተቋማት ብቃትና የትኩረት አቅጣጫ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ ዕውቀትን ለመለየት፣ ለመጠቀምና ተጨማሪ ዕውቀትን ለማመንጨት ያላቸው አቅምም ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ በኢኖቬሽን ሥርዓቱ ውስጥ ያሉት ተዋንያን ሁሉም የዳበረ አቅም ሊኖራቸውና ብሔራዊ የኢኖቬሽን ልማትን ያማከለ አቅጣጫ ሊያስቀምጡ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ድርጅቶች የሚመነጩ አዳዲስ ዕውቀቶችን የመለየትና የመጠቀም አቅም አናሳ ነው፡፡ ይህም አቅም በአመዛ’ የሚወሰነው የኢንተርፕራይዞች የሰው ኃይል ባለው ቀደምት ዕውቀት ነው፡፡ የሰው ኃይሉ መሠረታዊ ዕውቀት ፣ ክህሎትና ስለወቅታዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት  ያለው የግንዛቤ ደረጃ የኢንተርፕራይዞች አቅም ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡

ሌላው የኢንተርፕራይዞችን የኢኖቬሽን እንቅስቃሴ አመርቂ እንዳይሆን የሚያደርግ ሁኔታ ለኢኖቬሽን የሚውለው የመዋዕለ ነዋይ መጠን አናሳ መሆን ነው፡፡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ካላቸው ውስን የፋይናንስ አቅም የተነሳ በአዳዲስ ቴከኖሎጂዎች ላይ በስፋት መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ አዳዲስ ምርቶችን፣ የምርት ሂደቶችን ሲያስተዋውቁና አዳዲስ የማኔጅመንት ዘዴወችን ሲጠቀሙ አይታዩም፡፡ በነዚህ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ የምርምር ክፍሎችን ማየት የተለመደ አይደለም፡፡ አሉ የሚባሉት የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች መደበኛ ባልሆነ መልኩ ከምርት ተግባራት ጋር በተጓዳኝነት የሚከናወኑ ናቸው፡፡

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፣ በዩኒቨርሰቲዎችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ያለው ትስስር ደካማ በመሆኑ የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓቱ በተገቢው መጠን ጥቅም ሲሰጥ አይታይም፡፡ በኢኖቬሽን ተዋንያን መካከል ያለው ትስስር ደካማ ነው ማለት የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ፍሰት ዝቅተኛ መሆኑን የሚያመላክት ነዉ፡፡በመሆኑም በኢንተርፕራይዞች ውስጥ የሚከናወነው ውስን የኢኖቬሽን ጥረት ኢመደበኛ በሆነ መልኩ በሚገኝ እውቀትና በልምድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ድርጅቶች የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓቱ ተጠቃሚነት ደረጃም  በጣም ዝቅ ያለ ነው፡፡ይህም የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓቱ ለኢኖቬሽን ሥርዓት ግንባታ ተገቢውን አስተዋፅዖ እንዳያበረክት አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ለኢኖቬሽን ልማት የሚኖረው አስተዋፅዖ የጎላ እዲሆን ሌሎች የኢኖቬሽን ተዋንያን ትስስር ለማጠናከር የሚረዱ ፖሊሲዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ድርጅቶችን የሰው ኃይል ልማትና የምርምር መጠንና አቅጣጫ የሚወስኑ ፖሊሲዎች ትስስሩን ለማጥበቅ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ከነዚህ በአቅርቦት በኩል ያሉ ሁኔታዎችን ከሚወስኑ ፖሊሲዎች በተጨማሪ በፍላጎት በኩል ያሉ ሁኔታዎችም አዎንታዊ ለውጥ አንዲያመጡ የሚረዱ ፖሊሲዎችም አስፈላጊ ናቸው፡፡ የነዚሀ ፖሊሲዎች መኖር አእምሯዊ ንብረት የቴክኖሎጂ የዕውቀት ፍላጎትን በማሳደግ ረገድ የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡

የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ስርዓት መኖር የሚፈጥራቸውን አመቺ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ውጤትን  ለማስመዝገብ የኢንተርፕራይዞቹ ማኔጅመንት የግንዛቤ ደረጃም ወሳኝ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ከተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ትብብርና የሚፈጥሩት ትስስር የተቃና የሚሆነውና ከአእምሯዊ ንብረት ሥርዓቱ የሚያገኙት ጥቅም ሊረጋገጥ የሚችለው  ማኔጅመንቱ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የአእምሯዊ ንብረት አስተዳዳርን ከገበያ ዉጤታማነት ስትራቴጂዎች ጋር አቀናጅቶ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ በአእምሯዊ ንብረት አስተዳደር ላይ አለማተኮር አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚኖራቸው የሽርክና ዕድሎች ፣ በኢንቨስትመንት የመሳብ አቅምና በቂ የፋይናንስ አቅርቦት መኖር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሶስተኛ ወገኖችን የአእምሯዊ ንብረት መብትን ለመጣስ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡በመሆኑም የዳበረ የአእምሯዊ ንብርት ግንዛቤ ያለው ማኔጀመንት የአእምሯዊ ንብረትን ያላከተተ የቢዝነስ ስትራቴጂ አይኖረውም፡፡

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS