የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የአለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት በመተባበር የባሕላዊ ሕክምናን በአእምሯዊ ንብረት ስርዓት በማስጠበቅ ባሕላዊ ሐኪሞች የገበያ ድርሻቸውን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በሚሆኑበት ዙሪያ ባህላዊ መድሃኒቶችን በአእምሯዊ ንብረት መብቶች በማስጠበቅ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ዕውን ማድረግ እና ሞዴል የባህል መድሀኒት ፋርማሲ በኢትዮጵያ በማቋቋም የንግድ ስራቸውን ለማመቻቸት ዓላማ ያደረገ አውደ ጥናት መስከረም 26/2015 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
የሀገራት ኢኮኖሚያዊ የመወዳደሪያ መስፈርቶች የተፈጥሮ ኃብቶች መሆናቸው ቀርቶ የሰው ልጆች ዕውቀት ኃብቶች እየሆኑ መምጣታቸውን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኤርምያስ የማነብርሃን (ፒኤችዲ) በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ ተቋማቸው ከጎንደር ዩኒቨርስቲ እና ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚገኙ የባህል ሐኪሞች የባህል ሕክምና ዕውቀታቸውን ከአእምሯዊ ንብረት ስርዓት ጋር በማስተሳሰር እና የሕክምና ውጤታቸውን በአእምሯዊ ንብረት በማስጠበቃቸው የገበያ ድርሻቸው እንዲሰፋ አስችሏቸዋል በማለት አክለው ተናግረዋል፡፡
የአእምሯዊ ንብረት የንግድ፣ የቴክኒክ እና የህግ ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ ባለመብቶች በሶስቱም ዘርፎች ራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል፡፡ የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅትን በተለይ የLDC ክፍልን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን እንዲሁም በባህል ሕክምና ዘርፍ ይህ ውጤት እንዲገኝ ላደረጉ ባለድርሻዎች በሙሉ ባለስልጣኑ ያመሰግናል ብለዋል፤ ዋና ዳይሬክተሩ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለመብቶችን አሁን ባለው የአእምሯዊ ንብረት ስርዓት ተጠቅመው መብታቸውን ማስጠበቅ እንዲችሉና የገበያ አድማሳቸው እንዲሰፋ ከማድረጉም ባሻገር የማህበረሰብ ዕውቀት ህግን በማዘጋጀት ለመንግስት እንዲቀርብና የመልክዓ ምድር አመላካች ህግ ጥናትን ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተገልፆል፡፡ የባህል ሕክምና ውጤቶቻቸውን በአእምሯዊ ንብረት ስርዓት ያስጠበቁ የባህል ሐኮሞች የገበያ ድርሻቸው ከ140% በላይ ማሳደግ እንደቻሉ በቀረበው ጽሁፍ ተመላክቷል፡፡