የመብት ጥሰትን ለመከላከል የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ሚና

የኮፒራይት ኢንዱስትሪ በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን መጠበቅና ማልማት አስፈላጊ ነው፡፡ የአዕምሯዊ ንብረት መብት የሚያስገኙ የፈጠራ ስራዎች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በሚገባ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህግ ስርዓትን ማበጀትና ጠንካራ የህግ ተፈፃሚነት ስርዓትን መዘርጋት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊሰራባቸው ከሚገቡ በርካታ ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

በአንድ አገር የፍትህ ስርዓት ውስጥ ህግን በማስፈፀም ግንባር ቀደም ከሆኑ አካላት ውስጥ አንዱ ፖሊስ ነው፡፡ ፖሊስ አንድ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን በማስመልከት ጥቆማ ሲደርሰው ወይም መረጃ ከማንኛውም አካል በመቀበል ወይም በግል ተበዳይ አማካኝነት አቤቱታ ሲቀርብለት ወንጀል ስለመፈፀሙ ምርመራ የማድረግና ወንጀልን በመከላከል የህብረተሰብን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ከፖሊስ ስልጣን ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንዱ ጉዳይ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡

ጠንካራና አስተማማኝ አቅም የተፈጠረበት የኮፒራይት ኢንዱስትሪ ለመገንባት በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡በዚህ መነሻነት በተለያዩ ስውር ቦታዎች በተደራጀ አኳሃን የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል የመብት ጥሰትን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ደግሞ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡የኮፒራይት ኢንስፔክሽን አተገባበርን አስመልክቶ ጥሩ ተመክሮ ካላቸው አገራት መካከል ኬንያንና ናይጄሪያን እንደማሳያ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል ፡፡

በ2001 ዓ.ም በኬኒያ ፓርላማ ፀድቆ በወጣው ህግ መሰረት የኮፒራይት ቦርዱ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮችን የመቅጠር ስልጣን አለው፡፡የቦርዱ አባላት ወይም ማንኛውም የፖሊስ አባል የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች የተሰጣቸውን ስልጣን መነሻ በማድረግ የኢንስፔክተሮችን ተግባር ሊያከናውን ይችላል ፡፡

በኬንያ ኮፒራይት ህግ ላይ በተቀመጠው መሰረት ማንኛውም ግለሰብ እያወቀ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮችን ከስራቸው ለማደናቀፍ ወይም ለማወክ የሚሞክር ወይም ህጉ ባስቀመጠው ስርዓት መሰረት የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ድጋፍ ወይም መረጃ በሚፈልጉበት ጊዜ ለመተባበር ፈቃደኛ ያለሆነ ወይም የተሳሳተ መረጃ የሰጠ ግለሰብ አስከ ሃያ ሺህ በሚደርስ የኬንያ ሺሊንግ ወይም እሰከ ስድስት ወር ሊደርስ በሚችል እስራት ወይም በጣምራ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች የመብት ጥሰት መፈፀሙን ለማረጋገጥ ወይም ጥርጣሬ ሊያሳድር በሚችል ሁኔታ የመብት ጥሰት ሊፈጸም ይችላል ብለው ካመኑ የፍ/ቤት ትዕዛዝ (warrant) በማውጣት በየትኛውም ቤት ወይም ቦታ (premises)፣ መርከብ፣ አውሮፕላን ወይም ተሽከርካሪ ውስጥ የመግባትና የመበርበር፤ህገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጸምባቸው ዕቃዎችን፣ የፈጠራ ስራዎችን አቅፎ ሊይዝ የሚችል ጥቅል የሆነ ነገር ወይም ሰነዶችን የመያዝ ብሎም አስሮ የማቆየት ስልጣን አላቸው፡፡ ዕቃዎችንም አስረው ሲያቆዩ ለባለቤቱ በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን ኢንስፔክተሮቹ በቅንነት ለፈፀሙት ድርጊት ተጠያቂ አይሆኑም፡፡ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ለሚያደርሱት ኃላፊነት ግን ተጠያቂ እንደሚሆኑ በህጉ ውስጥ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ በአንፃሩ የናይጄሪያ የኮፒራይት ህግን ስንመለከት የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ስልጣንና ተግባር የቅጂና ተዛማጅ መብት በሚያስገኙ ሰራዎች ላይ የሚፈጸም የመብት ጥሰትን በመቆጣጠር ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡

በአሁን ወቅት ጥበቃ በሚደረግላቸው የፈጠራ ስራዎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት ያልተቀረፈ ችግር ከመሆኑም በላይ በህገ-ወጥ ድርጊት ላይ በመሰማራት የወንጀል ድርጊት በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በጣም አናሳ ነው፡፡ የአዕምሯዊ ንብረት የሆኑ የፈጠራ ስራዎች ካላቸው ልዩ ባህርይና ውስብስብነት አንፃር በዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ በቂ የህግ ዕውቀት ላለው ኢንስፔክተር ዕውቅና መስጠት ጠቀሜታው የላቀ ነው፡፡የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች የመብት ጥሰትን ለመቀነስ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ የመብት ጥሰት እንደተፈፀመ ጥርጣሬ ባለባቸው ቦታዎች ምርመራቸውን ለማድረግ በግልፅ የተደነገገ የህግ ስልጣን የሚሰጣቸው ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጪ እንዳይጠቀሙና የዜጎችን መሰረታዊ መብት እንዳይጥሱ የኢንስፔክተሮች  ስልጣንና ኃላፊነት  በህግ የተገደበ (የተወሰነ) ነው፡፡ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የመብት ጥሰት (copyright infringement) ተፈጽሟል ተብሎ በታመነበት ቦታ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት በማንኛውም ምክንያታዊ ጊዜ (reasonable time) የመግባት፣የመፈተሽና የመበርበር እንዲሁም ሌሎች መሰል ተግባራትን በማከናወን የመብት ጥሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ውጤታማ ስራ እንደሚያከናውኑ በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ  ነው፡፡ 

በዚህ ፅሁፍ ውስጥ እንደዋቢ ከተወሰዱ አገራት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መረዳት እንደሚቻለው የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች የሚያከናውኑትን ስራ ፖሊሶችም ከመደበኛ ስራዎቻቸው ጎን ለጎን ተግባራዊ የሚያደርጉት ሲሆን በዚህ በበለጠ ግን የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች በዘርፉ ላይ ልዩ ክህሎት(specialize) እና ልምድ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ለፖሊስ ከተሰጠው ስልጣን ጋር የሚጋጭ ሳይሆን የመብት ጥሰትን በሚፈለገው ደረጃ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች የተሻለ የቴክኒክ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው በመሆኑ በኮፒራይት ላይ የሚፈጸም የመብት ጥሰትን የመቆጣጠር ተግባር በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ 

በአጠቃላይ የኮፒራይት ኢንስፔክተሮች ስልጣንና ኃላፊነት በኮፒራይት ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከሉ ላይ ያተኮረ ብቻ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ስለሆነም በእኛም ሀገር የኮፒራይት ኢንስፔክተሮችን ስልጣንና ተግባር በህግ በመወሰን ጽ/ቤቱ እያዘጋጀ በሚገኘው የተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ የህግ ረቂቅ ውስጥ በማካተት ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባዋል፡፡

በኮፒራይትና ማህበረሰቦች ዕውቀት ጥበቃና ልማት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

ምንጭ፡

  • Copyright Act, Chapter 130, Laws of   Kenya Published by the National Council for Law Reporting with the Authority of the Attorney-General, Revised Edition 2012.
  • Enforcement Bulletin, Available online at < https://www.copyright.go.ke/copyright-enforcement.html > accessed on 4 March   2021
  • Copyright Act, Cap C28, Laws of the Federal Republic of Nigeria, 2004
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS