የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በአእምሯዊ ንብረት ምንነትና በምዝገባ ስርዓት ዙሪያ ከሀረሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ለመጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጥር 25/05/2014 ዓ.ም ልምዱን አካፈለ፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት በክልሉ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች ጥበቃ እንዲያገኙና ለሀገራዊ ልማት እንዲውሉ ልምድ ለመቅሰም ለተገኘው ቡድን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን አላማ፣ አደረጃጀትና ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመተግበር ላይ በሚገኙ ስራዎች ዙሪያ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በአእምሯዊ ንብረት ምንነት፣ በዘርፉ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች ምዝገባ ለማድረግ በሚያስፈልጉ መስፈርቶች፣ የምዝገባ ሂደት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የየዘርፉ ኃላፊዎች አጫጭር ማብራሪያዎችን አቅርበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረበላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተተርሰው ላቀረቡት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች ጥበቃ እንዲያገኙና የልማት አንቀሳቃሽ መሳሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ በክልሉ የአእምሯዊ ንብረት ዘርፉን የሚመራ አደረጃጀትና የሰው ሃይል መፍጠር እንደሚገባ ምክትል ዳይሬክተሩ በማጠቃለያ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በቴክኖሎጂ፣ በንግድ ምልክትና በቅጅ መብት የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች እና የማህበረሰብ እውቀቶች ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ የአእምሯዊ ንብረት ዘርፉን በአግባቡ ማደራጀትና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አክለው ተናግረዋል፡፡