በመልክዓ ምድር አመልካች ምርቶች ፕሮጀክት አተገባበር ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የመልክዓ ምድር አመልካች ምርቶች ፕሮጀክትን በበላይነት ከሚያስተባብረው የፈረንሳይ የግብርና ምርምርና ዓለማቀፍ ትብብር ድርጅት (CIRAD) ተወካዮች ጋር የፕሮጀክቱን አስተዳደር ጉዳዮችና ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት በቀጣይነት መከናወን ስለሚገባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ዛሬ ህዳር 08/2015 ዓ.ም ውይይት አካሄደ፡፡
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክትር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ፒኤችዲ) የመልክዓ ምድር አመልካች ምርቶችን በአእምሯዊ ንብረት ለማስመዝገብ እንዲሁም የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግና የአምራቾችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዳ የድጋፍ ማግኛ ፕሮጀክት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ ለተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ለድጋፍ ማግኛው ፕሮጀክት ምላሽ ከሰጡ ለጋሽ ድርጅቶች መካከል የፈረንሳዩ የልማት ድርጅት (AFD) የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ተቀብሎ ሲመረምር ከቆየ በኋላ ፕሮጀክቱን በገንዘብና በሙያ ለመደገፍ ስምምነት ላይ መድረሱን አክለው ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ለዚሁ ሥራ ድጋፍ ለማድረግ በዋና ዳይሬክተሩ የተቋቋመውና ከተለያዩ ክፍሎች የተውጣጣው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትም የተሳተፉ ሲሆን በፕሮጀክቱ አስተዳደር ዙሪያና የፕሮጀክቱን አተገባበር ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በCIRAD ተወካዮች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ፕሮጀክቱን ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስፈልጉ የዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ይህ የመልክዓ ምድር አመልካች ምርቶች ፕሮጀክት ከተተገበረና የታለመለትን ዓላማ ካሳካ እስካሁን ባለ ልዩ ጣዕም ምርቶችን ለማስጠበቅ ስንጠቀምበት ከነበረው የወል ንግድ ምልከት አሠራር በተጨማሪ አዲስ የሕግ ማዕቀፍና የአሠራር ሥርዓት በማስተዋወቅ የሀገራችንን የመልክዓ ምድር አመልካች ምርቶች ( ጥራታቸው/ መለያቸው ከሚመረቱበት ቦታ ጋር የተቆራኘ ምርቶች) በማምረትና በመሸጥ የተሰማሩ አምራቾችን እና የንግድ ተዋናዮችን በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ለምርቶችና አገልግሎቶች ሀገር አቀፍና አለማቀፍ የጥበቃ አማራጭ እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡