ለፈጠራ ባለሙያዎች ትልቅ ብስራት

ለፈጠራ ባለሙያዎች ትልቅ ብስራት የፈጠራ ባለመብቶች ስራዎቻቸውን ወደ ምርትና ንግድ ለመቀየር የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ የአእምሯዊ ንብረት ትመና እና የፋይናንስ አቅርቦት አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን ለበርካታ ባለድርሻዎች እና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አበርክቶ ያለው አሰራር ትኩረት ማግኘቱ ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የአእምሯዊ ንብረት ዋጋ ትመና (IP Valuation) እና የፋይናንስ አቅርቦትን አስመልክቶ ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ተቋማትና ከፈጠራ ባለሙያዎች ጋር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ምክክር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ይህንና ሌሎች በርካታ ስራዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጽ/ቤቱ ጋር በመተባበር ንግድ ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር 5 በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር አይነት እንዲያውሉት የሚያዝ መመሪያ ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም አወጥቷል፡፡ በዚህም ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና አስይዘው የሚበደሯቸውን ንብረቶች የኢንሹራንስ ተጠቃሚ በሚያደርገው የማይክሮ ኢንሹራንስ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ቋሚ የሆኑ ንብረቶችን ብቻ በማስያዝ የሚሰጠውን የብድር ስርዓት የሚቀይረው ይህ መመሪያ በተለይ የፈጠራ ባለሙያዎችን፣ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው መበደር የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ይህ የብድር ስርዓት ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራ ባለመብቶች ሆነው የፈጠራ ስራቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የፋይናንስ እጥረት ለሚገጥማቸው ባለመብቶችም ይሁን ለሀገሪቱ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ዕድገት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን አስምረውበታል፡፡

Share this
CONTACT US

Email : info@eipa.gov.et
Address:

+251 115 52 80 00
+251 115 52 72 02
Fax:-  +251 115 52 92 99
Po.Box:- 25322/1000

USFULL LINKS